‎በጤና ተቋማት ባገኙት የተሻለ አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን በኣሪ ዞን የዎባ አሪ ወረዳ ተገልጋይ እናቶች ተናገሩ

‎በጤና ተቋማት ባገኙት የተሻለ አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን በኣሪ ዞን የዎባ አሪ ወረዳ ተገልጋይ እናቶች ተናገሩ

በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የታገዘ የወሊድ አገልግሎት የእናቶችና ህፃናት ሞት ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የዞኑ ጤና መምሪያ ገልጿል፡፡

‎አስተያየታቸዉን ከሰጡን እናቶች መካከል ሲዳማ ማንዴላና ማናለሽ ተይዳኪ በጋራ በጤና ኬላ የቅድመ ወሊድ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዉ ወደ ዉብ ሐመር ጤና ጣብያ ማቆያ ገብተዉ በባለሙዎች አስፈላጊዉ ድጋፍና እገዛ ተደርጎላቸዉ ባገኙት የወሊድ አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡

‎የዉብ ሐመር ጤና ጣብያ አዋላጅ ነርስ ሀብተማርያም ስማቸዉ በእናቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ የጤና ችግሮች በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ በመሆናቸዉ ማቆያ ላይ ላሉ ነብሰጡት እናቶች ለራሳቸዉም ሆነ ለልጆቻቸዉ ደህንነት አስፈላጊዉን የቅድመ ወሊድ ክትትልና ምርመራ በማድረግ በሰለጠነ ባለሙያ የወሊድ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

‎የእናቶና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በጤና ጣብያዉ የቀዶ ህክምና አገልግሎት መሰጠት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከዚህ ቀደም ከጤና ጣብያዉ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን በሪፌር ወደ ጅንካ ሆስፒታል በሚልኩበት ወቅት ይደርሱ የነበሩ ችግሮች ተቀርፈዉ አንድም እናት በወሊድ ምክንያት እንዳልሞተች የሚናገሩት የቀዶ ህክምና ባለሙያ ናስር አለንጃ ናቸዉ ፡፡

‎የዎባ አሪ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ነፃነት በልሁ በበኩላቸዉ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ በተሰሩ የግንዛቤ ስራዎች እናቶች በጤና ኬላም ሆነ በማቆያ ላይ አስፈላጊዉን ቅድመ ወሊድ ክትትል በማድረግ ከዚህ ቀደም ከነበረዉ አሁን ላይ በሰለጠነ ባለሙያዎች የሚደረገዉ የወሊድ አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም እየተመዘገበ ነዉ ፡፡

‎የአሪ ዞን ጤና መምርያ ኃላፊ አቶ በድሉ በጊማስ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በተሰሩ በርካታ ስራዎች ነብሰ ጡር እናቶች ወደ ማቆያ መግባት ባህል እየሆነ በመምጣቱ በጤና ተቋማት በሰለጠነ ባለሙያ የሚውልዱ እናቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣጡን ገልጸዉ ለእናቶች የሚያስፈልጉ የግበዓት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡

‎አዘጋጅ፡- በናወርቅ መንግስቱ