በገጠርና በከተማ ያሉ የስራ እድሎችንና ፀጋዎችን በአግባቡ በመለየት ለዜጎች ክህሎት መር የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ

በገጠርና በከተማ ያሉ የስራ እድሎችንና ፀጋዎችን በአግባቡ በመለየት ለዜጎች ክህሎት መር የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የ2018 በጀት አመት ያለፉት 4 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እንዲሁም በአዳዲስ እሳቤዎችና የሪፖርት ስርዓት ላይ የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትልና የገጠር ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተመስገን ሀይሌ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ በክልሉ ያሉ የስራ አማራጮችንና ፀጋዎችን በመለየት ክህሎት መር የስራ ዕድሎችን ለዜጎች ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ለዚህም በገጠርና በከተማ ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ራስን ከመቻል ባለፈ በግለሰብ፣ በቤተሰብና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በብድር ስርጭትና አመላለስ ላይ ያሉ ውስንነቶችን መቅረፍ ይገባል ያሉት ሃላፊው፤ ከተለመዱ አሰራሮች በመላቀቅ ወጣቶችን ወቅቱን በሚመጥን በአዳዲስ የሪፎርም እሳቤዎች ማሰልጠንና ማላመድ ይገባል ብለዋል፡፡

በየአካባቢው ያሉ ምቹ ዕድሎችንና ፀጋዎችን በአግባቡ መለየት እንደሚገባ የገለፁት አቶ ተመስገን፤ በአደረጃጀትም ሆነ ከአደረጃጀት ውጭ የሚፈጠሩ ስራዎችን የመለየት፣ የመከታተልና የመደገፍ ስራ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ያሲን፤ መንግስት ለዜጎች በገጠርና በከተማ በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ሪፎርሞችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም በዞኑ በ2017 በጀት አመት በከተማና በገጠር ዘርፍ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የገለፁት አቶ ሙራድ፤ በዘርፉ የተጀመሩ ሰላም ስራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የበጀት አመቱ የዘርፉ ያለፉት 4 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በአዳዲስ እሳቤዎችና የሪፖርት ስርዓት ላይ የተዘጋጀ ስልጠና ለተሳታፊዎች ተሰጥቷል፡፡

ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሽና ማብራርያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተፈራ በየነ ከጉራጌ ዞን እና ወ/ሮ ፋንታዬ ተክለማርያም ከየም ዞን በሰጡት አስተያየት፤ መሰል ስልጠናዎች መዘጋጀታቸው በዘርፉ የወጣቱን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ከፍ ከማድረግ ባሻገር በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ውጤታማነት የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በተለይም በገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል የቢሮ ሃላፊዎች፣ የቢሮ የማኔጅመንት አባላት፣ ከክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡ መሀሪ አብድልከሪም – ከወልቂጤ ጣቢያችን