በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሴቶች የልማት ህብረትን ማጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ

በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሴቶች የልማት ህብረትን ማጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ

ቢሮው ‎የ2ኛ ዙር ሞዴል የሴቶች ልማት ህብረት የስራ እንቅስቃሴ በመገምገምና የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀትና አሰራር ማንዋል፣ ብሐራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገት ፖሊሲ እና የህይወት ክህሎት ላይ ያተኮሩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ኩሪባቸው ታንቱ መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት፤ በክልሉ በ23 ወረዳዎች በሚገኙ 69 ቀበሌያት ከ32 ሺህ በላይ የሴቶች የልማት ህብረት መኖራቸውን ጠቅሰው 2 ሺ 224 ሞደል ማህበራትን ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የሴቶች የልማት ህብረት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ስላለው ምርጥ ተሞክሮዎችን ቀምሮ ወደ ሌሎች የሴቶች ልማት ህብረቶች እንዲስፋፉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

‎ሞዴል የሴቶች የልማት ህብረቶቹ በቁጠባ፣ በገቢ ማስገኛ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከል አንጻር በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።

የሴቶች የልማት ህብረትን በይበልጥ ከተጠቀምን ዘርፈ ብዙ ችግር የምንፈታበትና የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በማሳለጥ የሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ መሰረት እንደሆነ ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጠናከር ቅንጅታዊ ስራ እንደሚያስፈልግና የተሻለ ተግባር የፈጸሙ ሴቶችን ተሞክሮ በማስፋት ሌሎች አዳዲስ ህብረቶችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ሴቶችን በጓሮ አትክልት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በቡና ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በቅመማ ቅመም ልማት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማሰማራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡም ተገልጿል።

በመድረኩ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሞደል የልማት ህብረቶች ዕውቅና ተሰጥቷል።

በምክክር መድረኩ የ12 ዞኖች፣ 3 ሪጂዮ ፖሊሲ ከተሞች ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አመራሮችና ከተመረጡ ወረዳዎችና ቀበሌያት የተውጣጡ ሞደል የሴቶች ልማት ህብረት አመራሮች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን