ንድፈ ሀሳብ በተግባር ሲፈተን

ንድፈ ሀሳብ በተግባር ሲፈተን

በአስፋው አማረ

የመረብ ኳስ ስፖርት እንደ ባህል የሚዘወተርበት ከምባታ ጠምባሮ ዞን ዛሬ ላይ በእግር ኳሱም ቢሆን ከሀገር አልፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነች እንስት እግር ኳስ ተጫዋች ማፍራት ችሏል፡፡ ሎዛ አበራን፡፡

ሌሎች በወንዶችም ሆነ በሴቶች በክለብ፣ እንዲሁም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ተጫዋቾችን አፍርቷል፡፡ ለእነዚህ ተጫዋቾች ውጤታማነት ተፈጥሮ ከለገሳቸው ተሰጥኦ ጎን ለጎን ምክንያት የሆኑ በርካታ አሰልጣኞች መኖራቸው እሙን ነው፡፡

ከከፍተኛ ውጤት ጀርባ አሰልጣኞች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ አሰልጣኞች ለተጫዋቾች የሚያስተላልፏቸውን መልዕክቶች በመቀበልና በመተግበር የነገውን ማንነታቸውን በመገንባት ረገድ ተጫዋቾችም እንዲሁም ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡

በዛሬው ስፖርት ዝግጅታችን የሀምበርቾ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ አስራት ዮሐንስ የሕይወት ታሪክ እንዳስሳለን፡፡

ወደ አሰልጣኝነት ከመግባቱ በፊት ከልጅነቱ ጀምሮ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ነበር ያሳለፈው፡፡ ከ13 ዓመት በታች በፕሮጀክት በመታቀፍ ሲሰለጥን ቆየ፡፡ በሜዳ ውስጥ በሚያሳየውም እንቅስቃሴ ልምድ እያካበተ ዞኑን ወክሎ በክልሎች የክለቦች ሻምፒዮን ላይ እስከመሳተፍ ደርሷል፡፡

በወቅቱ ባሳየው ድንቅ ብቃት በደቡብ ፖሊስ ክለብ ጥሪ ተደርጎለት ነበር። ጥሪውን ተከትሎ በሰዓቱና በቦታው ቢገኝም ካጋጠመው ጉዳት የተነሳ መሰለፍ አልቻለም። ከጉዳቱም ፈጥኖ ባለማገገሙ እድሉን ለማጣት ተገደደ፡፡

ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ያደረገው ትምህርቱ ላይ ነበር፡፡ መማሩንም ቀጠለ፡፡ የሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ በመቀላቀል በ2003 ዓ.ም በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል በዲፕሎማ ተመረቀ፡፡ እንዲሁም ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ የትምህርት ዘርፍ ተቀብሏል፡፡

ከተመረቀም በኋላ በስፖርት ሳይንስ መምህርነት ማገልገል ጀመረ፡፡ ለሁለት ዓመታት በመምህርነት ካገለገለ በኋላ ከማስተማሩ ጎን ለጎን በ2005 ዓ.ም የሀምበርቾ ሴቶች እግር ኳስ ክለብን ማሰልጠን ጀመረ፡፡

የዛሬው የሀምበርቾ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ቀድሞ በዱራሜ ከተማ አስተዳደር ስር ነበር፡፡ በ2013 ዓ.ም በዞን ታቅፎ ዛሬ ላይ ፕሪሚየር ሊግ መግባት የቻለ ክለብ ሆኗል። በዚህ ውስጥም የአሰልጣኝ አስራት አስተዋጽኦ አይዘነጋም፡፡

ወደ አሰልጣኝነት ስትገባ የገጠሙህ ችግሮች አልነበሩም ወይ? ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ ሲመልስ፦

“በርካታ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ በተለይም የሴቶች አሰልጣኝ ሲኮን፡፡ እኔን ብዙ ችግሮች ናቸው የገጠሙኝ፡፡ የሴቶችን ቡድን ወደ ክለብ ደረጃ ለማሳደግ እና ከ2005 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም ከፍተኛ ሊግ እስከምንገባ ድረስ እጅግ ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍነው፡፡

“ዓመቱን ሙሉ ሴቶች እና ወንዶች እኩል ዝግጅት ሲያደርጉ ይቆያሉ፡፡ ለሴቶች በጀት የለም ተብሎ ከውድድር ውጭ እንሆናለን። እንደዚህ ዓይነት ችግር ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለ ነው፡፡ አሁን ላይ በተወሰነ ደረጃ እየተስተካከለ ነው ማለት ይቻላል።

“በዚህ ጊዜ ድካሜ ከንቱ ሲሆንና በምን ደረጃ ላይ እንዳለሁ ሳላውቅ ስቀር ሁኔታው ያማል፡፡ የልጆቹም ድካም ከንቱ ሆኖ ሲቀር ማየት ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ህመም ይፈጥራል፡፡ ይህ ጊዜ በጣም አስቸጋሪና ከባድ ነበር፡፡” ብሎናል፡፡

አሰልጣኝ አስራት ሀምበርቾ ሴቶች እግር ኳስ ክለብን በአጋጣሚ አልያዘውም፡፡ ከታች ጀምሮ ያሳደገው ክለብ ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ክለቦች ውድድር የጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡

ይሄኔ ነበር ለአሰልጣኝ አስራት ዕድል በሩን ያንኳኳችለት፡፡ በዚህ ጊዜ የደቡብ ክልል ሴቶች እግር ኳስ ክለቦች ውድድር በዱራሜ ከተማ ላይ ተካሂዶ ነበር፡፡ እድሉንም በመጠቀም የክልሉን ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ማንሳት ቻለ፡፡

ክለቡም የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ደቡብ ክልልን በመወከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊ ሆኗል። በአሰልጣኝ አስራት እየተመራ ቡድኑ በኢትዮጵያ ደረጃ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል። በ2014 ዓ.ም ክለቡ የሴቶች ከፍተኛ ሊግን ተቀላቅሏል።

በከፍተኛ ሊግ ቆይታችሁ ምን ይመስል ነበር? ለሚለውም ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፦

“በ2014 ዓ.ም የነበሩብንን ክፍተቶች እና ጠንካራ ጎኖችን በሚገባ ከለየን በኋላ ነበር የ2015 ዓ.ም ውድድር የጀመርነው፡፡ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማካተት ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ችለን ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ነበር ሊጉን በተቀላቀልንበት ብዙም ሳንቆይ በሁለተኛ ዓመታችን ወደ ፕሪሚየር ሊግ የገባነው።

“በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈው ነው ለውጤት መብቃት የቻልነው፡፡ ዛሬ ላይ ሳወራው ቀላል ይመስላል፡፡ ግን ሁሉም ነገር አሁን ላይ ታሪክ ሆኗል፡፡ ሌላ ድል ለማጣጣም እራሴን በማዘጋጀት ላይ ነኝ” ሲል ያለፈበትን ጊዜ አስታውሶናል፡፡

አሰልጣኝ አስራት ባለፉት የውድድር ጊዜያት ከቡድኑ ጋር ሻምፒዮን ለመሆን ብርቱ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ በአንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶችና በተጨዋቾች የልምድ ማነስ ችግር፣ ማግኘት የሚገባቸውን ነጥቦች በማጣት አንደኛ ደረጃን ሳይዙ ቀርተዋል። ይህም ቢሆን በስተመጨረሻ አሰልጣኝ አስራት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የመግባት ህልሙን እውን አድርጎለታል።

ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጋችሁን ስታረጋግጡ ያለው ስሜት ምን ይመስል ነበር? ስንል አስከትለን ጠየቅን፦

“በፍጹም ማመን ይከብድ ነበር፡፡ ከታች ጀምሮ ተሰርቶባቸው የመጡ ተጫዋቾችን ነው የተጠቀምኩት፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሳተፍ ማለት ደግሞ የሚኖረው ደስታ ወደር የለውም፡፡

“በተለይም ደግሞ ሊጉ ከመጠናቀቁ በፊት ቀሪ ጨዋታዎች እያሉ ነበር ወደ ፕሪሚየር ሊግ መግባታችንን ያረጋገጥነው፡፡ ይህም አንደኛ ሆነን ባናልፍም ከምንም በላይ እፎይታን ይሰጣል፡፡

“ይህ ውጤት ለእኔ ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ በተለይም ደግሞ ከታች ምንም ከሌለበት በመነሳት ለዚህ ድል መብቃት ቀላል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን የልፋቴን ውጤት ያየሁበት ቀን በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል” ሲል የነበረውን የድል ስሜቱን አጋርቶናል፡፡

በቀጣይም ሰፊ የሆነ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው፡፡ እንደ አሰልጣኝ ሊጉን መቋቋም የሚችሉ ተጫዋቾችን የማብቃት ሥራን ይከውናል፡፡ ለዚህም ቢሆን ውስን ተጫዋቾችን ማስፈረም የመጀመሪያ ስራው እንደሆነ ገልጿል፡፡ በአሁኑ ስዓት ወደ እዚህ ስራ ለመግባት የመጀመሪያ የክለቡን ከፍተኛ የደመወዝ መጠን መታወቅ እንዳለበት ይናገራል፡፡

ምክንያቱም ክለቡ የሚደገፈው በመንግሥት በጀት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው። ከዚህም የተነሳ የተለያዩ የመንግስት አካላት ውሳኔን የሚፈልግ ነው፡፡

የዞኑ ህብረተሰብ ለስፖርቱ ያለው ፍቅር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገረው አሰልጣኝ አስራት “በሴትም በወንድም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉ ታሪካዊ ክስተት ነው” ሲል ተናግሯል፡፡

የሴቶችም የወንዶችም ቡድን ባስመዘገበው ውጤት ክለቡን ለመቀበል ክልሉም ሆነ ዞኑ ያደረገው ድጋፍ እና አቀባበል መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም ይላል፡፡ በቀጣይ ክለቦቹ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው እንዲቀጥሉ ሰፊ የሆነ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።