የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ የእግር ኳስ ፕሮጀክት ሰልጣኞች ሀገራቸውን በእግር ኳስ የመወከል ራዕይ እንዳለቸው ተናገሩ

የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ የእግር ኳስ ፕሮጀክት ሰልጣኞች ሀገራቸውን በእግር ኳስ የመወከል ራዕይ እንዳለቸው ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በእግር ኳስ ስልጠና ታግዘው አካባቢያቸውንና ሀገራቸውን በእግር ኳስ የመወከል ራዕይ እንዳለቸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ማዕከል የእግር ኳስ ፕሮጀክት ሰልጣኞች ተናገሩ።

ሰልጣኞቹ ሀገር አቀፍ የታዳጊ ህጻናት ፕሮጀክት ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ዕድል እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

ቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ዕድሜቸው ከ13 እና ከ15 አመት በታች የሆኑ 50 ህጻናትን በመያዝ የእግር ኳስ ፕሮጀክት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ከሰልጣኞቹ መካከል ዳግም ወንድሙና አበኔዘር ወንድማገኝ በሚሰጣቸው ስልጠና ታግዘው የእግር ኳስ ክህሎታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል።

ከመሰል አቻ ፕሮጀክቶች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን በእስካሁኑ ከአንድ ጨዋታ የአቻ ውጤት በስተቀር ተሸንፈው እንደማያውቁ ገልጸው፤ ሚዛን አማን ታዳጊ የእግር ኳስ ፕሮጀክት ቡድንን 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፋቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ በተጠናቀቀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክለቦች እግር ኳስ ውድድርም ከዋንጫ ጨዋታ ቀደም ብሎ የቦንጋ ግራዝማች ጳውሎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታዳጊዎች ፕሮጀክትን 2ለ1 ከማሸነፋቸው ባለፈ በሳዩት ድንቅ ችሎታ ከስፖርት ማህበረሰቡ አድናቆት ተችሯቸዋል።

ቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ለሚያደርግላቸው ድጋፍ ያመሰገኑት ታዳጊዎቹ ከአከባቢው አልፎ በሀገር አቀፍ ውድድሮች ተሳትፈው አቅማቸውን ለመፈተሽ የሚያስችል ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

“በመሠል የታዳጊ ፕሮጀክቶች ህጻናት ሲታቀፉ የወላጆች ሚና የጎላ ሊሆን ይገባል” ያሉት ደግሞ የሰልጣኞቹ ወላጆች ናቸው።

አቶ አጥናፉ ወልደገብርኤል፣ መምህርት ትዕግስት አስራትና ወይዘሮ ገነት ያዕቆብ እንደተናገሩት ልጆቻቸው ጊዜያቸውን በእግር ኳስ ሜዳ ማሳለፋቸው በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ እንዲሁም በሥነ-ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

ይህን ስልጠና ሳይሰላቹ በመስጠት ላይ ለሚገኙት አሰልጣኝ ምስጋና ያቀረቡት ወላጆች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛነታቸውን ገልፀው ሁሉም እንዲደግፋቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የፕሮጀክቱ አሰልጣኝ በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ የስፖርት ክፍል ረዳት መምህር ቴዎድሮስ ካሳ ህጻናትን ማሰልጠን ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ከአካባቢያቸው አልፈው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግና ከፍተኛ ሊግ መጫወት የቻሉ የእግር ኳስ ተጫዎቾችን ያፈራ ፕሮጀክት መሆኑን አሰረድተዋል።

አሁንም ከ13 አመት እና ከ15 ዓመት በታች የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 50 ህጻናትን በመያዝ እያሰለጠኑ መሆናቸውን በመጠቆም በህፃናቱ ችሎታ እንደሚደነቁና ለወደፊት ትልቅ ደረጃ ደርሰው የመመልከት ተስፋ እንዳላቸው አክለዋል።

የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ዲን አቶ አንተነህ አየለ በበኩላቸው ኮሌጁ ከመደበኛ መማር ማስተማር ጎን ለጎን በኮሌጁ እግር ኳስ ፕሮጀክት ለታቀፉ ልጆች የመጫወቻ ሜዳ በማመቻቸት፣ የስፖርት ሙያተኛ በመመደብና አቅም በፈቀደ መጠን የቁሳቁስ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም ህጻናቱን ለመደገፍ ኮሌጁ ዝግጁ መሆኑን ያነሱት አቶ አንተነህ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በክልሉ ስፖርቱን ከሚመሩ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ጥረት ይደረጋልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ድንቃየሁ ዮሐንስ – ከቦንጋ ጣቢያችን