ዩኒቨርሰቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ተገለጸ

ዩኒቨርሰቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት እና አጋርነት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “ለመቀናጀት እንወያይ፣ ለለውጥ እንስራ” በሚል መሪ ቃል ለስድስኛ ጊዜ የማህበረሰብ የምክክር ፎረም በይርጋጨፌ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን፥ የማህበረሰቡን ችግር ገባ ብሎ በማየት ችግሮችን ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርገው ጥረት አመሰግነዋል።

የዲላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኤልያስ ዓለሙ የአርንጓዴ ዩኒቨርስቲ መለያ የሆነው ዲላ ዩኒቨርስቲ፥ በመልካም ስነ-ምግባርና እውቀት የታነጹ ወጣት ምሁራንን ማፍራቱን ጠቁመው፥ የተለያዩ የማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጤና፣ በግብርና፣ በተፈጥሮ ሀብትና በትምህርት ዘርፍ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ተሳታፊዎች መፍጠንና መፍጠርን ተግባራዊ ለማድረግ ፎረሙ የቤት ስራዎችን ለመከፋፈል ይረዳል ብለዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተግባር የሳይንስ ዩኒቨርሲት ለመሆን እየሰራን መሆኑንም አመላክተዋል።

በምክክሩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር)፥ ተቋማት የአሰራር ስርዓት ዘርግተው ለህዝቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ሀገራችን እየሰራች ነው ብለው የዲላ ዩኒቨርስቲም በአራቱ የትኩረት መስኮች ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ መሆኑ አበረታች እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዩኒቨርስቲው አንጋፋነት አንጻር በርካታ ተግባራት ይጠበቅበታል ያሉት ዶ/ር ዝናቡ፥ ከትምህርት አንጻር ስብራቱን ለመጠገን ዩኒቨርሰቲው የቤት ስራ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን