ወንጀልን በመከላከልና የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ ፖሊስ ሚናውን መወጣት እንዲችል መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

ወንጀልን በመከላከልና የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ ፖሊስ ሚናውን መወጣት እንዲችል መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

የኮሚሽኑ የ2018 በጀት የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን በቦንጋ ከተማ ገምግሟል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ባለፉት ጊዜያት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተሰሩ ሥራዎች በጸጥታው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ሀገር የመጣውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተከትሎ የሚፈጠሩ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል የፖሊስ ተቋም በቴክኖሎጂ፣ በመረጃ እና ቴክኒክ የተሟላ ተቋማዊ አቋም እንዲኖረው ማደራጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

ወንጀል መከላከል የብዙ ወገን ነው ያሉት አቶ አንድነት፤ ፖሊስ በሰብዓዊነት ከማገልገል አኳያ ከፍ ያለ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሳ በበኩላቸው፤ የትራፊክ አገልግሎት፣ የወንጀል ምርመራ እና የመረጃ ጥራት፣ የአከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ እንዲሁም ያልተገባ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የመሳሰሉ ችግሮች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ስር ነቀል ማሻሻያ በማድረግ የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወንጀልን የመከላከል ተግባር የህዝቡን ድጋፍ የሚጠይቅ ነዉ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት መተባበር እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የፓትሮል ቅኝት ሥራዎችን በማጠናከር ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የክልሉ ፖልስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል እና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኮሚሽነር አስናቀ ሀብቴ ናቸው።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና ሀሰተኛ የብር ኖት ዝውውር፣ የደን ውጤቶች፣ የምግብ ሸቀጦች፣ ቡና እና የመሳሰሉ ምርቶች ዝውውር በሀገር ሰላምና ኢኮኖሚ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አስገንዝበዋል።

የሙስና፣ የታክስ ማጭበርበር፣ የደንብ መተላለፍ ወንጀሎችም በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ አወንታዊ ተዕጽኖ ያላቸው በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

በክልሉ ሁሉም ዞኖች የተካሄደው የፖሊስ ተቋማትን የማጥራትና መልሶ የማደራጀት ግምገማ ውጤትና ቀጣይ ተግባራት ላይ የጋራ ምክክር በማድረግ መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን