ሀዋሳ፣ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን እንደሚሆን በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎች ማሳያ ናቸው ሲሉ የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ገለፁ፡፡
የኢፌድሪ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልልና የልዩ ወረዳው የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ በክላስተር የለማ የበቆሎ ማሳን ጎብኝተዋል።
የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን እንደሚሆን በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ በኩታ ገጠም በበቆሎ ሰብል የተሸፈነው ማሳ ማሳያ ነው፡፡
ይህንን የመሰለ ተስማሚ የአየር ፀባይ ፣ መሬትና መልካም ምድር ይዘን እኛ ሌሎችን የምንረዳ እንጂ ከሌሎች እርዳታ የምንጠብቅ መሆን የለብንም የሚለው የሁል ጊዜ ቁጭታችን ነበር ያሉት አቶ አዲሱ በሀገሪቱ በምርት ዘመኑ የመኸር እርሻ ብቻ ከ20 ሚልየን በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑንና ከዚህም ውስጥ ከ12 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር መልማቱን ጠቁመዋል።
ይህም በመደመር እሳቤ በጋራ በመዝራት፣ በመንከባከብና በመሰብሰብ ውጤታማ የግብርና ስራ ለመስራት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ሀገርም ሆነ በቀቤና ልዩ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ ተግባራት የኢትዮጵያን ማንሰራራት ዕውን የሚያደርጉ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል ።
በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤታማነት በሪፓርት ከመገምገም ባሻገር በአካል መጎብኘት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ናቸው፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ በ2017/18 የምርት ዘመን በበልግ እርሻ 12,500 ሄ/ር መሬት በኩታ ገጠም በበቆሎ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን 1ነጥብ 2 ሚልየን ኩንታል የበቆሎ ምርት እንደሚጠበቅ የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ተናግረዋል ፡፡
ዘጋቢ፣ ጅላሉ ፈድሉ ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በቀቤና ልዩ ወረዳ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱ ተገለጸ
ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን መስራት ያሉ ችግሮችን ቀርፎ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ የመንግስትና የህዝብን ሀብት የሚያድን በመሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ