ሀዋሳ፣ መስከረም 30/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቀቤና ልዩ ወረዳ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የልዩ ወረዳው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ፅ/ቤት ገልጿል፡፡
በልዩ ወረዳው በሴቶች ልማት ህብረት የተደራጁ ሴቶች በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ በመሰማራታቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ፈቲያ ሱልጣን በልዩ ወረዳው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀት ከ13 ሺህ 5መቶ በላይ ሴቶችን መንግስት ባመቻቸው ከ10 ሄክታር በላይ መሬት ላይ በ10 የልማት ህብረት በመፍጠር በግብርና ዘርፍ በመሰማራት እያለሙ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በልዩ ወረዳው ሴቶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የቁጠባ ባህላችው እንዲያጎለብቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ሀላፊዋ በተለይ በገጠርም ሆነ በከተማ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት መስክ እንደ ጓሮ አትክልት፣ ዶሮና ከብት እርባታ እንዲሁም በወተት አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በልዩ ወረዳው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ የልማት ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የጠቀሱት ወ/ሮ ፈቲያ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት ማለት ቤተሰብን ማብቃት በመሆኑ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ሴቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሀሊሃ ኑረዲን በበኩላቸው በልዩ ወረዳው ሴቶችን በልማት ቡድን በማደራጀት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀቤና ልዩ ወረዳ ፈረጀቴ ቀበሌ የሙልዱ ሴቶች ልማት ህብረት ሰብሳቢ ወ/ሮ ቀመሪያ ሙህዲን ከዓመታት በፊት ገንዘብ ቆጥበው የልማት ስራ እንዲያከናውኑ ልዩ ወረዳው ሶስት ሄክታር መሬት በማመቻቸቱ በቆሎ ጤፍና ሌሎች ሰብሎች በመዝራት በአሁን ወቅት ከ180 ሺ ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
የልማት ህብረቱ አባላት የቁጠባ ባህላቸውን በማጎልበት ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ከመፍታት ባለፈ በአካባቢያቸው የተቸገሩ ሴቶችን በመደገፍ ሰብአዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡
የሙልዱ ልማት ህብረት አባላት በሰጡት አስተያየት በአሁን ወቅት በቀበሌው የቆሎና ጤፍ ማሳቸውን በአግባቡ በመንከባከብ የተሻለ ምርት ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው የልማት ህብረቱ አባል በመሆናቸው ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ተላቀው ቤተሰባቸውን ማስተዳደር መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
በቀቤና ልዩ ወረዳ ሩሙጋ ቀበሌ የቆንካም የእንቁላል ዶሮ እርባታ አባል ወ/ሮ ሙንሳ ከድር ከስደት ተመልሰው ከሴቶቹ ጋር በጋራ በመስራት ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው መደራጀት አንዱ ያለውን አቅም ለሌላው በማጋራት ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሚናው የላቀ ነው ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሙኒሳ ሴቶች የስራ ዕድሉን ካገኙ በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ጠቁመው ከስደት ይልቅ በሀገራቸው ሰርተው ሀብት ማፍራት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፣ ተዘራ በቀለ
More Stories
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን እንደሚሆን በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎች ማሳያ ናቸው – ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን መስራት ያሉ ችግሮችን ቀርፎ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ የመንግስትና የህዝብን ሀብት የሚያድን በመሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ