ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን መስራት ያሉ ችግሮችን ቀርፎ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ የመንግስትና የህዝብን ሀብት የሚያድን በመሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ

ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን መስራት ያሉ ችግሮችን ቀርፎ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ የመንግስትና የህዝብን ሀብት የሚያድን በመሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ

‎በደቡብ ኦሞ ዞን የወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የ2018 ዓ.ም የበጋ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማብሰሪያና የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ተግባር የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።

‎በዞኑ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ91 ሚሊየን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ማዳን መቻሉም ተመላክቷል።

‎በመድረኩ ተጋባዥ እንግዳ የሆኑት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ማካተት ተሳትፎ ንቅናቄ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በረከት በርገላ፤ በክልሉ በወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ተግባራት መከናወናቸዉን ገልፀዋል።

‎በደቡብ ኦሞ ዞንም በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካማና አረጋዊያን የተደረጉ የቤቶች ግንባታና እድሳት፣ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የተደረጉ የቁሳቁስ ድጋፍ፣ በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ጥበቃ ስራ፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ማስወገድና በሌሎች የትኩረት መስኮች ላይ የተከናወኑ ተግባራት ዉጤታማና የሚበረታቱ በመሆናቸዉ አመራሩም ሆነ ወጣቶቹ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

‎የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት የህሊና እርካታን የሚሰጥና በፈጣሪ ዘንድም የተቀደሰ ተግባር ነው ያሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፤ ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን መስራት ያሉ ችግሮችን ቀርፎ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባሻገር የመንግስትና የህዝብ ሀብትን የሚያድን በመሆኑ በክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎችን ባህል አድርጎ በበጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል።

‎አክለዉም የዞኑን ወጣቶች በ18 ትኩረት መስኮች በማሳተፍ በተለይ የበርካታ አቅመ ደካማና አረጋዊያን እንባን ያበሰ ከ867 በላይ የአዲስ ቤት ግንባታና ጥገና፣ በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ከ400 ዩኒት በላይ ደም በመለገስና በሌሎች የትኩረት መስኮች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

‎በቀጣይ በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

‎የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥጋቡ ጎሮጊ፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች እዉቀታቸዉን፣ ጉልበትና ጊዜያቸውን በማህበረሰቡ ዉስጥ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት በመሆኑ በዞኑ በተለዩ የትኩረት መስኮች ከ145 ሺ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ543 ሺ በላይ የህበረተሰብ ክፍሎችን በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በዚህም ከ91 ሚሊየን በላይ የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ማዳን መቻሉን አስረድተዋል።

‎ያነጋገርናቸዉ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላትም በጎ ስራ በመስራት የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ደስታና የህሊና እርካታን የሚሰጥ በመሆኑ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰሩ ዉጤታማ ስራዎችን በበጋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

‎በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰሩ ስራዎች ሪፖርትና የበጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎት እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሷል።

‎በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፣ የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ፣ የመምሪያ የስራ ኃላፊዎች፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

‎የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላትና መዋቅሮች የሰርተፊኬት፣ የሜዳልያ፣ የዋንጫና የቴሌቭዥን ሽልማት ተበርክታል።

‎ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን