በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቁ ዜጋ ለማፍራት እየተከናወነ የሚገኘው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፣ መስከረም 30/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቁ ዜጋ ለማፍራት እየተከናወነ የሚገኘው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በዳዉሮና ኮንታ ዞኖች የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አመራሮችና አሰልጣኞች ገለጸዋል፡፡
ላለፉት 10 ቀናት በታርጫ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና መጠናቀቁ ተገልጿል።
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በሥራ ገበያ ሙያዊ ብቃት እንዲሁም ወቅቱን የሚመጥን ክህሎትና አቅም ያላቸው ተወዳዳሪ አሰልጣኞችን ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛል።
ይህንን ተግባር የበለጠ ለማሣካት እንዲቻል በክልሉ ታርጫ ክላስተር ከዳዉሮና ኮንታ ዞኖች የተወጣጡ ከ2 መቶ 35 በላይ አሰልጣኞች “ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት” በሚል መርህ ቃል ሥልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናውን ከተካፈሉ አሰልጣኞችና ዲኖች መካከል የጪዳ ኢንዲስትሪያል ኮሌጅ ዲን ይርጋለም ምታ፣ የቶጫ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን ጌዴዎን ኤርምያስ እና ከገሣ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አሰልጣኝ በረከት አካሉ በጋራ በሰጡት አስተያየት ወቅቱን የሚመጥን የሰው ኃይል ለማፍራት እንዲቻል የአመራርና አሰልጣኝ አቅም ማሣደግ ወሳኝ በመሆኑ በጥብቅ ዲስፕሊን መከታተል መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ሥልጠናው በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የአመራርነት ብቃትን በማሣደግ የመማር ማስተማር ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ከበደ በበኩላቸው ሥልጠናው መነሻ ያደረገው በአሰልጣኞች ዘርፍ የሚታየውን የክህሎት ክፍተት ለመሸፈን እንዲያስችል ነው ብለዋል፡፡
ከተሰጣቸው ሥልጠና አሰልጣኞቹ የደረሱበትን ለመለየት ይቻል ዘንድ ምዘና በመስጠት የተጠናቀቀ እንደሆነም ነው አቶ ዮሴፍ ያብራሩት።
የታርጫ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ኤፍሬም አይሳ እንደሚሉት በኮሌጁ ከዳዉሮና ኮንታ ዞኖች ከሚገኙ 6 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተገኙ አሰልጣኞች እንደአገር ብቁና የተሻለ ሥራ ፈጣሪ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል በተግባር የታገዘ ሥልጠና ነው።
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ አሰልጣኞች ሥራ አጥነትን እንዲቀረፍ እየተሠራ የሚገኘውን ተግባር በብቃትና በጥራት እንዲወጡ የሚያስችል ሞራል የሚሰጥ ስልጠና እንደሆነም ነው የገለፁት።
መሳይ መሰለ ፦ ከዋካ ቅርንጫፍ
More Stories
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን እንደሚሆን በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎች ማሳያ ናቸው – ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
በቀቤና ልዩ ወረዳ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱ ተገለጸ