የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት ማስመዝገብ የሚችል  ባለብዙ ፀጋ ክልል ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት ማስመዝገብ የሚችል  ባለብዙ ፀጋ ክልል ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

‎ሀዋሳ፣ መስከረም 30/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት ማስመዝገብ የሚችል ባለብዙ ፀጋ ክልል ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡

ዱቡሻና የዱቡሻ ወጋ ስርዓትን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚረዳ የምክክር መድረክ  በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ  ይገኛል፡፡

‎በመርሀ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደርጉት  የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) ፤ የዱቡሻ ወጋ ስርዓት የተደበቀ እውነት የሚወጣበት ፣ ሠላም የሚሰበክበት ፣ የባህል ተቋም ነው ብለው ይህንን ስርዓት የሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት በዩኔስኮ የአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል ።

‎ሀገራችን ኢትዮጵያ  ሪፎርም ካደረገች ወዲህ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ አውስተው  በቱሪዝም ዘርፍ  እመርታን እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።

‎በጋሞ ብሔረሰብ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ ከሚገኙ ባህላዊ ዕሴቶች አንዱ የዱቡሻ ወጋ ነው ያሉት ደግሞ የኢፌድሪ የቅርስ ጥናት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያለው ናቸው ።

‎እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የኢፌዴሪ መንግስት ለቅርስ ጥበቃና ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየለሙ ለአገልግሎት እየበቁ ይገኛሉ ብለዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት ማስመዝገብ የሚችል ባለብዙ ፀጋ ክልል ነው ብለው ከእነዚህ መካከል የዱቡሻ ወጋ ስርዓት ሰላምን ለማፅናት ፣ ፍቅርን ለመትከል ከፍተኛ አበርክቶ አለው ብለዋል።

‎ቅርሶችን ከመንከባከብ እና ከመጠበቅ ባሻገር ታፍነውና ተሸሽገው የቆዩ ፀጋዎችን ወደ ሀብት የመቀየር ተግባር ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ያወሱት አቶ ጥላሁን ፤ የጋሞ ዱቡሻ ወጋ ስርዓት ወንድማማችነትን ፣ ፍቅርን እና አንድነትን ለመገንባት አበርክቶው ከፍ ያለ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

‎ዘጋቢ ፦ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን