በየደረጃው የሚገኙ ላብራቶሪዎችን አቅም በማጎልበትና በማቀናጀት የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ሀይሉ (ዶ/ር) ገለፁ
የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በሚገኘው የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስራ እንቅስቃሴዎችንና የአሰራር ሂደቶችን ምልከታ አድርገዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር መሳይ ሀይሉ (ዶ/ር) ከምልከታው በኋላ ባደረጉት ውይይት አንደተናገሩት፤ በየደረጃው የሚገኙ ላብራቶሪዎችን በሙሉ አቅም ለመደገፍ የሚያስችል ምልከታ መደረጉንና እንደሀገር የላብራቶሪ አቅም ለመገንባት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
እንደ ሀገር ወደ 5ሺ የሚሆኑ ላብራቶሪዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መንግሥት ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ላብራቶሪዎችን ለማጠናከር ርብርብ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ላብራቶሪዎችን በማዘመን የተሻለ የጤና አገልግሎት በመስጠት የጨቅላ ሕጻናትና የእናቶች ሞት ቅኝትና ምላሽ ላይ ትኩረት ለመስጠትና ለመደገፍ የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለሟሟላት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው፤ በክልሉ ላብራቶሪ ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ መቆየቱን አንስተው ለዚህም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር አብራርተዋል።
እንደ ክልሉ የሰዎች አሰፋፈር ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖሩና በዚህም ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነት ሰፊ በመሆኑ ተከታታይ ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል።
በምልከታው የተገኙት በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ታደለ ቡራቃ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ የላብራቶሪ አቅም ለማጎልበት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን አንስተው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስራ እንቅስቃሴና የተደረገውን ሪፎርም አድንቀዋል።
ከፌደራል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተለያዩ ግብዓቶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ይድነቃቸው ደዳቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
በመስክ ምልከታው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ፣ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ታደለ ቡራቃ፣ ሌሎች የፌደራል ጤና ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮችና የክልሉ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮች የተገኙ ሲሆን በወራቤና ቡታጅራ ሆስፒታሎች ተመሳሳይ ምልከታ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ: መልካሙ ታፈሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን እንደሚሆን በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎች ማሳያ ናቸው – ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
በቀቤና ልዩ ወረዳ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱ ተገለጸ