ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ በመሆን ዜጎች ቀልጣፋና ተደራሽ ፍትህ እንዲያገኙ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያውንና መሠረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥን ተግባራዊ በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአሪ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ገለፁ

ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ በመሆን ዜጎች ቀልጣፋና ተደራሽ ፍትህ እንዲያገኙ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያውንና መሠረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥን ተግባራዊ በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአሪ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ገለፁ

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሥሩ ከሚገኙ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምና 2018 በጀት ዓመት ጠቋሚ እቅድ ላይ የጋራ ምክክር በጂንካ ከተማ አካሂዷል።

የአሪ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ አንተነህ በላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ በመሆን ዜጎች ቀልጣፋና ተደራሽ ፍትህ እንዲያገኙ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያውንና መሠረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥን ተግባራዊ በማድረግ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ኃላፊው አክለውም እንዳሉት፤ የሕዝቡን የፍትህ ጥያቄ ከመመለስ አንፃር በበጀት አመቱ የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር ደካማ አፈፃፀምን በማረም የፍትህ መዛነፍን ለማስተካከል ይሠራል።

ቀልጣፋ ተደራሽና የተገልጋይ እርካታ ያለውን የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት የዳኝነት ሥራውን ከሌሎች የፍትህ አካላት በቅብብሎሽ ሊሠራ ይገባል ያሉት የአሪ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትልና አበቱታ መስማትና መወሰን ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ሽመልስ፤ በውስንነት የተነሡ ሀሳቦችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ርብቃ እሳቱ፤ ምክር ቤቱ ተቋማትን በሦስት ዘርፍ ከፍሎ የሚደግፍበት ሂደት መኖሩን ጠቅሰው የሕዝቡ የፍትህ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል::

የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚቀረፉበት የለውጥ ሥራዎችን በማጠናከር እና የመዝገብ ክምችትን ለመቀነስ የተሠራው ሥራ ለተሻለ ውጤት እንዳበቃቸው የመድረኩ ተሳታፊዎችና ተሸላሚዎች ገልፀዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ያመጡ ተቋማትና ፈፃሚዎች ተመዝነው የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን