የቀደምት ትወልድ ታሪክ፣ ባህልና እሴትን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለፀ
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የሴክተር ጉባኤና የ2018 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ አመት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ ዳርጌ ተክሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የቀደምት ትውልድ ያቆዩትን ታሪክ፣ ባህልና እሴት በመጠበቅና በማልማት ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ማህበረሰብ ክፍል ሃላፊነት እንደሆነና የዚህ አንድ አካል የሆነውን ቋንቋ ማሳደግና ማጠናከር ይገባል።
ከመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ጎን ለጎን ነባር የሆነውን የጀፎረ እሴትን በመጠበቅ ከሃገር ቅርስነት ባሻገር አለም አቀፍ ቅርስ እንዲሆን ጠብቆ ማስቀጠልና ለትውልድ ማሸጋገር እንደሚገባም አቶ ዳርጌ አሳስበዋል።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው፤ በ2017 በጀት አመት መምሪያው የጉራጌን ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና የቱሪዝም አቅሞችንና የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዘምነውና ተውበው የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
መስቀልና አረፋ በጉራጌ፣ ነቅወ እና ኩርፍወን የአደባባይ በዓላት እንዲሆኑና በቀጣይነት ለተመራማሪዎች በሚጠቅም መልኩ ተሰንደው ከባህል ብረዛ ተጠብቀው እንዲቀመጡና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲሻገሩ ሰፊ ስራ ተሰርቷል ሲሉ ሃላፊዋ ተናግረዋል።
የገጠር ኮሪደር መሰረትና ተምሳሌት የሆነው የጀፎረ ልማት ስራን ሁሉን አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝና ከሃገር አልፎ አለም አቀፍ ቅርስ እንዲሆን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ተመዝግቦ የጉራጌን ታሪክና ባህል ጎልቶ እንዲታይ ወደ ነባር ይዘቱ የመቀየር፣ ውበቱ የመጠበቅና ህገወጥ የአጥር ግንባታዎችን በመከላከል ከ4 መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ለምቶ ለቱሪስት ክፍት ተደርገዋል ሲሉ ወ/ሮ መሰረት ገልፀዋል።
ቋንቋ መናገር፣ መጠቀምና ማጥናት ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ አይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለፁት ሃላፊዋ፤ በዚህ መሰረትም የጉራጊኛ ቋንቋን የሚዲያና የስራ ቋንቋ እንዲሆን በዞኑ ምክር ቤት ለወሰደው ቁርጠኝነት ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ገልፀዋል።
የቱሪዝም ሴክተር በሐገር ደረጃ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን በማንሳት በዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ያለውን የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች በሚፈለገው መልኩ የገቢ ምንጭ በመሆን ማህበረሰቡ የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ወ/ሮ መሰረት አመላክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በበጀት አመቱ የዞኑን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልና የቱሪዝም ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ አበረታች ስራ መሰራቱን ጠቁመው በቀጣይ ከጀፎረ አጠባበቅና ልማት ጋር በተያያዘ የሚታይ ውስንነት ማስተካከል እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመድረኩ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ባህልና የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የሚያሳይ የሚያስተዋውቅ ዌብሳይት ሰርቶ አስረክቧል።
በመጨረሻም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የመምሪያው ባለሙያዎች፣ መዋቅሮችና ባለድርሻ አካላት ዕውቅና በመስጠትና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የግብ ስምምነት ከታችኛው መዋቅሮች ጋር በመፈራረም መድረኩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ፡ ፍስሀ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን እንደሚሆን በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎች ማሳያ ናቸው – ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
በቀቤና ልዩ ወረዳ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱ ተገለጸ