በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቀነስ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለጸ
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመቀነስ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
የዞኑ ፍርድ ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በሚቀጥሉ አምስት ዓመታት መሪ ዕቅዶች ዙሪያ የባለድርሻ አካላት መድረክ በይርጋጨፌ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ፤ በ2017 በጀት ዓመት የዞኑ አስተዳደር ከፍትህ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በቡና እና ሌሎች ምርቶች ላይ የሚሰተዋሉ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሀገር ብሎም በክልል ደረጃ የተጀመረውን የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሸን ተግባራዊ የማድረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፤ ቅሬታ የተነሳባቸውን ዳኞች በጊዜያዊነት ከሥራቸው በማገድ የማጣራት ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሴቶችና ህጻናት የሚደርሱ መጠነ ሰፊ የወንጀል ድርጊቶች መስተዋላቸውን የጠቆሙት አቶ ሳሙኤል፤ ችግሮችን ለመቀነስ ወንጀለኞች ላይ ከሚወሰደው የእርምት እርምጃ በተጨማሪ በቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ በስፋት መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ምስጋና ዋቃዮ በበኩላቸው፤ መንግስት ፍትህ እንዳይዛባ ለአቅመ ደካሞች ነጻ የጥብቅና አገልግሎት በመስጠት ፍትህን ለማስፈን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት ሴቶችና ህጻናት አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን የፍትህ ጥያቄ ከመመለስ አኳያ ክፍተቶች መስተዋላቸውን አንስተዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የነበሩ ጉድለቶችን ለማረም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባ የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ እንደ ሀገር የተጀመረውን የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ውጤታማ ለማድረግ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቀነስ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለጸ

More Stories
በስልጤ ዞን የሚገኘው ሃይረንዚ ልዩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2017 የትምህርት ዘመን በሃገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ውጤቱ እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላደረጉ መምህራን የማትጊያና የእውቅና ፕሮግራም ተካሄደ
የዋካ ቅርንጫፍ ጣቢያ ወቅታዊና ጥራት ያለውን መረጃ ተደራሽ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ