የጭንቀት ህመም (anxiety disorder) እና መፍትሄዎቹ

የጭንቀት ህመም (anxiety disorder) እና መፍትሄዎቹ

ጭንቀት የሰው ልጅ ከሚሰማው የተፈጥሮ ስሜት ዉስጥ አንዱ ሲሆን በዕለት ተዕለት ኑሮዉ በተለያዩ ምክንያቶች ሊጨነቅ ይችላል። ጭንቀት በፍርሀት የሚገለፅ የስሜት አይነት ነው፡፡

የጭንቀት ህመም ከመደበኛ ወይም ከተለመደው ጭንቀት የተለየ ደስ የማይል ፍርሀትና የፍርሀቱ መነሻ ምክንያታዊ ሳይሆን ሲቀር እንዲሁም ጭንቀቱን መቆጣጠር ሲያቅት የዕለት ከዕለት ክዋኔዎች ለመከወን ሲከብድ ረዘም ላለ ማለትም 6 ወርና ከዚያ በላይ ጊዜ በተከታታይ ቀጣይነት ኖሮት ሲቆይ የጭንቀት እክል (anxiety disorder) እንደሚባል በደ.ሬ.ቴ.ድ በ”ዋናው ጤና” የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት በይርጋለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ የሥነ-አዕምሮ መምህርና በሀዋሳ ዘፀዓት የአዕምሮ ህክምና መስራች ከነአን በለጠ ያስረዳሉ።

የሰውነት በላብ መጠመቅ፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ራሥ ምታት፣ የልብ ምት መጨመር፣ የድካም ስሜት መጨመርና ሌሎች መሰል ምልክቶች የጭንቀት ህመም የተለያዩ መገለጫዎች እንደሆኑ የሥነ- አዕምሮ መምህሯ ይጠቅሳሉ፡፡

የጭንቀት ህመም መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

  •  ከስነ-ልቦና ጋር የተያያዘ ከልጅነት ጀምሮ ያለ የአስተዳደግ ተጽእኖ
  •  ስነ-ሕይወት (biological) ማለትም በዘር (genetical)
  • አዕምሮ ለተለያዩ ተግባራት በሚጠቅማቸው ኬሚካሎች አመመጣጠን (neuro chemical imbalance) እና አዕምሮ ውስጥ ያለ መዋቅር (structure) ከተለመደው ቅርፁ ሲቀያየር
  • የአካላዊ፣ ጾታዊና ንግግር ጥቃቶች
  • የተለያዩ የኮኬይን፣ ሲጋራ፣ ሌሎች የአደንዛዥ ዕጽ ሱሶች

የሥነ-አዕምሮ መምህር ከነአን በለጠ፤ የተለያዩ የጭንቀት ህመም አይነቶች እንዳሉ አንስተው አብዛኛውን ጊዜ በህክምና ከሚያጋጥሙ ህመም አይነቶች ዉስጥ አንዱ አጠቃላይ የጭንቀት ህመም (Generalized anxiety disorder) ሲሆን በብዛት ታማሚዎቹም በአንድ ጊዜ ስለ ብዙ ነገሮች የማሰብና መጨነቅ መሞከር ከሚታይባቸው አንዱ ምልክት እንደሆነ ያብራራሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ እንቅልፍ አለመተኛት ከተኙ በኋላ ቶሎ ቶሎ መንቃት አንድ የጀመሩት ነገር ላይ ትኩረት አድርገው ለመጨረስ መቸገር የሰዉነት መገጣጠሚያ ክፍሎች ላይ የመዛል  ስሜት ይታይባቸዋል፡፡

ለጭንቀት ህመም አጋላጮች ከሚጠቀሱት መካከልም ጭንቀቱን ያሽለኛል በሚል ምክንያት የሚወሰዱ የአልኮል፣ ሲጋራ፣ ኮኬይንና የመሳሰሉ ሱሶች እንዲሁም ደም ግፊት፣ የልብ ህመምና የሆርሙን መቀያየር አንዱ በሽታ ለአንዱ አጋላጭና ጭንቀቱ በራሱ የነበረውን ችግር ሊያባብሰዉ እንደሚችል ያስረዳሉ።

ይህ አጠቃላይ የጭንቀት ህመም የምንለውና ሌሎች የጭንቀት ዕክል አይነቶች መሆኑን ከሚረጋገጡባቸው መንገዶች አንዱ የህመሙ ምልክቶች ለተከታታይ 6 ወርና ከዚያ በላይ ሲቆዩ የዕክሉ ተጠቂ እንደሆነ መታወቅ ይችላል።

በዚህም ጊዜ ወደ ህክምና መሄድ እንደሚያስፈልግና ህመሙ ዝም ከተባለ ታማሚዉ ብቻዉን ከማዉራት እስከ እብደት እንደሚደርስ የሥነ-አዕምሮ መምህሯ ይናገራሉ።

እንደ የሥነ-አዕምሮ መምህር ከነአን በለጠ ገለጻ ህመሙ በብዛት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ተጋላጭነታቸዉ ከፍ ያለ እንደሆነና በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች እንደሚጠቁ የዓለም ጤና ድርጅት ጥናቶች ያመላክታሉ።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት የጭንቀት ህመም ለተለያዩ ህመም የመጋለጥ ዕድልን እንደ ደም ግፊት፣ stroke፣ የጨጓራ ቁስለትና ተጓዳኝ የጤና ዕክሎች የመጋለጥ ዕድልን እንደሚጨምር ያመላክታል፡፡

  •  የማህበረሰቡ ግንዛቤ እና የህክምና መፍትሄዎቹ፡-

እንደ የሥነ-አዕምሮ መምህር ከነአን በለጠ ገለፃ ለጭንቀት ህመም ማህበረሰቡ የሚሰጠው ግንዛቤ አናሳ መሆን ህመሙን እንደ ህመም ያለመቁጠር ብሎም ከመንፈሳዊ ጋር አያይዞ መረዳት ታካሚዎቹ ህክምናው በሚሰጥበት ቦታ መታየት እንዲሁም ማንነታቸው እንዳይታወቅ የመፍራት ችግሮች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

የተለያዩ የጭንቀት ህመሞች እንደየህመማቸዉ አይነት ምልክቶች በተደጋጋሚ የሚታዩባቸው መሆኑ ሲረጋገጥ የህክምና ባለሙያ ጋር ቀርቦ በማማከር የትኛው አይነት ዕክል ነው የሚለውን በመለየት በባለሙያ ሀኪሞች ተለይቶ በሚዋጥ መድሀኒቶች (ክኒን) ወይም የንግግር (psyco therapy) የህክምና መንገዶች እንደ ማንኛውም ህመም በመታከም ወደ መደበኛ ጤንነት መመለስ እንደሚችል ይመክራሉ።

አዘጋጅ፡ ብዙነሽ ዘውዱ