ከ1 መቶ ሺህ ኩንታል  በላይ ጥራት ያለው ቡና  ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የኣሪ ዞን ዋና አስተዳደር ገለፁ

ከ1 መቶ ሺህ ኩንታል  በላይ ጥራት ያለው ቡና  ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የኣሪ ዞን ዋና አስተዳደር ገለፁ

ሀዋሳ፣ መስከረም 29/207 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ1 መቶ ሺህ ኩንታል  በላይ ጥራት ያለው ቡና  ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ገለፁ።

በዋና አስተዳዳሪው የተመራ የዞኑ አመራሮች በደቡብ ኣሪ ወረዳ በቡና ኢንዱስትሪዎች እየተከናወነ ያለውን ተግባር ተዘዋውረው ምልከታ አድርገዋል ።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በዚህን ወቅት እንደገለፁት በቡና  ኢንዱስትሪዎች ቡናን በአግባቡ በመፈልፈል፣ በማጠብና ልየታ በማድረግ ጥራቱ እንዲጠበቅ እየተሰራ ያለው ተግባር የተሻለ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ይህ ተግባር ለቡና ጥራትና የኣሪ ቡና ስያሜን ይበልጥ ለማረጋገጥ በዞኑ በሁሉም ኢንዱስትሪዎች በልዩ ትኩረት እንዲሠራ አቶ አብርሃም አሳስበዋል ።

የደቡብ ኣሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ኃይሌ ከአርሶ አደሩ የቡና አለቃቀም ጀምሮ ለቡናው ጥራት በልዩ ጥንቃቄ እየተሠራ እንዳለ አስረድተዋል።

ወረዳው በስፋት የቡና ምርት የሚገኝበት በመሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አርሶ አደሮች በክላስተር እንዲያለሙ በተላለፈው ግንዛቤ ልክ ተግባራዊ ሆኖ በአሁን ወቅት ምርቱ ደርሶ እየተለቀመ ተጠቃሚው አርሶ አደር በተሻለ ዋጋ ለቡና ማጠቢያ ኢንዱስትሪዎች እንዲያቀርብ እየተደረገ ነው ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

አጠቃላይ የቡናው ጥራት ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ ከመሆኑ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ ተጠብቆ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚታገኘውን የውጭ ምንዛሬ እንዲታረጋግጥ በልዩ ክትትል ሥራው እየተመራ እንዳለ የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ አስረድተዋል።

ዘንድሮ እንደዞን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የታሰበውን መጠን ማሳካት የሚያስችል ምርት መኖሩንም አቶ ጉራልቅ ተናግረዋል፤ ለቡና ጥራት ልዩ ጥንቃቄ መሰጠቱንም እንዲሁ።

የቡና ማጠቢያ ኢንዱስትሪ ባለቤቶችም ከርሶ አደሩ በጥራት በመረከብ ወደ ኢንዱስትሪዎች ገብቶ በተሻለ ጥራት ታጥቦ እንዲታሸግና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ በሀላፊነት እየተሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልፀዋል።

በኢንዱስትሪ ማሽኖች ተቀጥረው የሚሠሩና ሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው አካላትም የተሻለ ገቢ እያገኙ እንዳሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ህገ ወጥ የቡና ንግድና እንቅስቃሴ እንዳይኖር በግብረ ሀይል ቁጥጥር እየተደረገ እንዳለም ተገልጿል ።

በኣሪ ዞን 11 የቡና ማጠቢያ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉና በአሁን ወቅት ሥራ ላይ መሆናቸው ተጠቅሷል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ -ከጂንካ ጣቢያችን