ሀገሪቱ ለምታወጣው የልማት ፖሊሲና በዘርፉ ለሚታቀደው ዕቅድ ተዓማኒ መረጃዎችን ማሰባሰብ ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑ ተገለፀ
በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሆሳዕና ቅርንጫፍ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች ለተውጣጡ ከ1 ሺ 78 በላይ ለሚሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በሆሳዕና ከተማ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን አሰፋ፤ ስልጠናው ለኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መስክ ሰራተኞች በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የተሰጠ መሆኑን ጠቁመው ሀገራዊ የመረጃ አሰባሰብ ሂደትን ለማሳለጥ ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑን አመላክተዋል።
ስልጠናው በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተሰጠ መሆኑ የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ለሰልጣኞች የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ 1 ሺ 78 መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች በወራቤ ደግሞ 598 የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ወደ 70 የሚሆኑ አሰልጣኞችና ሌሎችም አስተባባሪ አካላት መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
መረጃው በሀገሪቱ የተለያዩ አምራች ድርጅቶች ተጨባጭ መረጃ ለማሰባሰብ የሚረዳ ከመሆንም ባሻገር በዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ለምታወጣው የልማት ፖሊሲና በዘርፉ ለሚታቀደው እቅድ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም አቶ ካሳሁን አመላክተዋል።
ስልጠናው ላለፉት 25 ቀናት የተሰጠ ሲሆን ሠልጣኞች ጥራት ያለውን መረጃ በተገቢው ማሰባሰብ እንዲችሉ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒከሺን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ዓለሙ በበኩላቸው፤ ተዓማኒና ወቅቱን ያገናዘበ የመረጃ ግብዓት ማግኘት ለተገቢ ሀገራዊ ውሳኔ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን አመላክተዋል።
ስልጠናው በተለያዩ የአምራች እንዱስትሪዎችና የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨባጭ መረጃዎችን ለማግኘት የሚረዳ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚሻ መሆኑን አመላክተዋል።
አንዳንድ የስልጠናው ተሳታፊዎችም በስልጠናው ባገኙት ግንዛቤ መሠረት የድርሻቸውን ሊወጡ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በስልጤ ዞን የሚገኘው ሃይረንዚ ልዩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2017 የትምህርት ዘመን በሃገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ውጤቱ እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላደረጉ መምህራን የማትጊያና የእውቅና ፕሮግራም ተካሄደ
የዋካ ቅርንጫፍ ጣቢያ ወቅታዊና ጥራት ያለውን መረጃ ተደራሽ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ