በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት እየተሻሻለ መምጣቱን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ

በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት እየተሻሻለ መምጣቱን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ
‎
‎በሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሟላ፣ ጥራቱን የጠበቀና ቀልጣፋ በማድረግ የሆስፒታሉን ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
‎
‎ለረዥም ዓመታት ከአጥንት ጋር በተያያዘ ለነበረባቸው ህመም ከአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ባገኙት አገልግሎት ከህመም መፈወሳቸውንና በዚህም በእጅጉ መርካታቸውን የገለፁት ወ/ሮ ሽብሬ ከበደ ናቸው፡፡
‎
‎የአጥንት ህክምና አገልግሎት በአርባምንጭ ሆስፒታል መጀመሩ በተለይ የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ላለባቸው እፎይታ ከመፍጠሩም በተጨማሪ እንግልትና ወጪን እንዳስቀረላቸው ገልፀዋል፡፡
‎
‎በህፃናት ተኝቶ ህክምና ክፍል ልጃቸውን እያስታመሙ የነበሩትን አቶ ኃይሉ ታደሰ ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት የተሻለ መሆኑን ጠቁመው አልፎ አልፎ የመድኃኒት እጥረት እንደሚስተዋል ጠቁመዋል፡፡
‎
‎ከወላድ ክፍል አግኝተን ያነጋገርናቸው ወ/ሮ ዘላለም ገበየሁ በበኩላቸው፤ አገልግሎት አሠጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በፅኑ ህሙማን ክፍል ጠቅላላ ሐኪም ‎ዶ/ር በረከትአብ ከበደ፤ ጥራቱን የጠበቀና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
‎
‎ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠውን አገልግሎት የተሟላ፣ ጥራቱን የጠበቀና ቀልጣፋ በማድረግ የሆስፒታሉን ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አምባቸው ዱማ ናቸው፡፡
‎
‎አክለውም በሆስፒታሉ ቀደም ሲል ተጀምረው የተቋረጡ አገልግሎቶችን የማስቀጠል፣ አዳዲሶቹን የማስጀመርና የማዘመን ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
‎
‎ዘጋቢ:፡ ተነሳ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን