“በምግብ ራስን መቻልን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ግቡ ያደረገ የግብርና ስራ እየተከናወነ ነው” – አቶ ማስረሻ በላቸው

“በምግብ ራስን መቻልን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ግቡ ያደረገ የግብርና ስራ እየተከናወነ ነው” – አቶ ማስረሻ በላቸው

“በምግብ ራስን መቻልን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ግቡ ያደረገ የግብርና ስራ እየተከናወነ ነው” ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ በ2017 ዓመተ ምህረት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የመደበኛ መስኖ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዕቅድ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን አጠናክሮ በማስቀጠል የምግብ ዋስትናን በሀገር ውስጥ ምርት ማረጋገጥ እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል።

የንቅናቄ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ፤ በምግብ ራስን ለመቻልና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ግቡ ያደረጉ የግብርና ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

አዳዲስ የስራ አቅጣጫዎች ተይዘው በሀገር ደረጃም ለልማት የሚሆኑ ሁሉም መሬቶች እየታረሱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ውጤታማ እየሆነ የመጣውን የበጋ መስኖ ስንዴ ውጤታማነት ያነሱት አቶ ማስረሻ፤ በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ እየመጣበትና ከውጭ የሚገባውን ምርትም እየተካ ይገኛል ብለዋል።

ዓመታዊ የስንዴ ሽፋን ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መድረሱን ጠቁመው፤ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ አስታውቀዋል።

የተፈጥሮ እርጥበትን ወይም ዝናብን በመጠቀና ሁሉንም የውሃ አማራጮች በመጠቀም ማልማት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ስራ ከሚለማው ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ320 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በበጋ መስኖ ስንዴ እና በ1ኛ ዙር የመስኖ ልማት በአትክልትና ስራስር ከ62 ሺህ ሄክታር በላይ ማሣ ይለማል ተብሏል።

ያለፈውን የበጋ መስኖ ስንዴ አፈፃፀምን እና የዘንድሮውን እቅድ በተመለከተ ሰነድ በክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ እየቀረበ ነው።

በመድረኩ የክልል የሁሉም ዞኖች፣ የወረዳዎች የዘርፉ ስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን