የዝርያ ማሻሻያ ዘዴ መጠቀም የወተት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ
የአርሶ አደሩ በዝርያ ማሻሻያ ዘዴ የመጠቀም እና የተሻሻሉ ከብቶችን የማርባት ግንዛቤ እያደረገ መምጣቱን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ።
አቶ ይስሐቅ ቡኬ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጋንታ ቦንኬ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የገዟትን ጥጃ በተሻሻለ ዝርያ ኮርማ በማስጠቃት የዝርያ ማሻሻያ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በዝርያ ማሻሻያ ዘዴ በማዳቀል ሁለት ጥጆችን ማግኘታቸውንና በዚህም የከብቶቻቸው ቁጥር አራት መድረሱን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የዚያው ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አማረች አሽሌ፤ የግብርና ባለሙያዎች በፈጠሩት ግንዛቤ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ከብቶች ማርባት መጀመራቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ ሁለት ጥጆችና አንዲት ላም እንዳላቸው ተናግረዋል።
አክለውም በዝርያ ማሻሻያ የሚወለዱ ጥጆች በአካል ትልቅና ጥሩ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በጋንታ ቦንኬ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት የእርባታ ባለሙያና የጽ/ቤቱ ተወካይ ወ/ሮ ታደለች ፍቃዱ፤ በቀበሌው የዝርያ ማሻሻያ ሥራው ተፈላጊና ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የእንስሳት ልማት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ታጋሽ ግርማ፤ እንስሳትን በማድራት ሥራ የተሻሻሉ ዝርያን ለማግኘት እየተሰራ ሲሆን በዚህም በ2018 በጀት ዓመት በ10 ቀበሌያት 406 ላሞችንና ጊደሮችን ለማዳቀል ታቅዶ ባለፈው ነሐሴ ወር 304 በማዳቀል 75 በመቶ መከናወኑን አስታውቀዋል።
የዝርያ ማሻሻያ ሥራ ዋና ዓላማው በአነስተኛ ቦታ ላይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ከብቶችን በማርባት ከብዛት የሚገኘውን ምርት ከጥቂቶች ማግኘት ነው የሚሉት ዶ/ር ታጋሽ፤ አርሶ አደሩ በዝርያ ማሻሻያው ተጠቃሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመሥራት ወቅቱን ጠብቀው የማዳቀሉን ሥራ ለመሥራት መታቀዱንም አክለዋል።
ዘጋቢ፡ ፍሬው ዲጋ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
የዝርያ ማሻሻያ ዘዴ መጠቀም የወተት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

More Stories
የተለያዩ የውሃ አጠቃቀም ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ
በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት እየተሻሻለ መምጣቱን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ
“በምግብ ራስን መቻልን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን ግቡ ያደረገ የግብርና ስራ እየተከናወነ ነው” – አቶ ማስረሻ በላቸው