በአለምሸት ግርማ
አፀደ ህፃናት ወይም የመጀመሪያው የልጅነት ትምህርት በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ለልጆች ሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚጣልበት ምዕራፍ ነው። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ መደበኛ ትምህርትን አንድ ብለው የሚጀምሩበት ስፍራም ነው። በዚያም የሚኖራቸው ቆይታ በህይወታቸው እና በትምህርታቸው ስኬት እንዲኖራቸውና ክህሎትን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
በመሆኑም ልጆች በዚህ የህይወት ክፍል ላይ የሚያገኙት ትምህርትና ክህሎት ለቀጣዩ ማንነታቸውም አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
በዘርፉ የሚሰሩ አካላትም ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በየዓመቱ ክረምት ላይ በትምህርት ቤቶቻቸው የአሰራር ማሻሻያንና እድሳትን ሲያደርጉ፣ አዳዲስ መምራንን ሲቀጥሩ እና መሰል ተግባራትን ሲከናውኑ ይስተዋላል።
ከምንም በላይ ግን አፀደ ህፃናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲወዱና ውጤታማ እንዲሆኑ መልካም መሰረት የሚጣልበት ስለሆነ መምህራኖች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።
የዛሬዋ እቱ መለኛችንም ከልጆች ጋር በርካታ ዓመታትን አገልግላለች። ረዳት መምህርነትና ዋና መምህርነት ያለፈችባቸው የስራ ዘርፎች ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቱ ውስጥ ምክትል ርዕሰ መምህርት ናት። ይህንን ማድረግ የቻለችው ስራዋን እየሰራች ጠንክራ በመማሯ ነው።
ትምህርት የለውጥ መሳሪያ በመሆኑ ከራሷ አልፋ በምትሰራበት የትምህርት ተቋም ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲገኙ የበኩሏን እያበረከተች ትገኛለች። በመማር ማስተማሩ ዘርፍ ያገኘችውን ተሞክሮ እንደሚከተለው አጋርታናለች።
መምህርት ለምለም ዳንኤል ትባላለች። ትውልድና ዕድገቷ ሃዋሳ ከተማ ነው። ለቤተሰቦቿ አምስተኛ ልጅ ናት። አስተዳደጓ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሲሆን፤ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ኢትዮ አሜሪካ እና ቢኤንቢ ትምህርት ቤቶች በመግባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች።
ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከተሸጋገረች በኋላ ዘጠነኛና አስረኛ ክፍሎችን በሃዋሳ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተለች ሲሆን፤ የመሰናዶ ትምህርቷን ደግሞ በሃዋሳ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላ አጠናቃለች።
በልጅነቷ መሆን የምትፈልገው ሀኪም ነበር። ሆኖም ግን የምትፈልገውን ማግኘት ባትችልም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ህይወቷን በተሻለ ሁኔታ እየመራች ትገኛለች።
በመንግስት ዩኒቨርሲቲ የምትፈልገውን የትምህርት ዘርፍ ማግኘት ስላልቻለች በግሏ በሃዋሳ ሪፈራል የጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በመግባት መማር ጀመረች። በዚህ ጊዜ ነበር ወደ መምህርነት ሙያ የምትገባበት አጋጣሚ የተፈጠረው። አሁን በምክትል መምህርነት የምትሰራበት ትምህርት ቤት፥ በወቅቱ የረዳት መምህር ማስታወቂያ ያወጣል።
ይህን ማስታወቂያ ስትመለከት መስራት እንዳለባት በማመን ለስራው አመለከተች። ስራው የሚፈለገውን መስፈርት በማሟላቷ እና ተቀባይነትን በማግኘቷ ስራውን ጀመረች። ቀስ በቀስም ሙያውን እየወደደችው፤ ራሷንም በትምህርት እያሳደገች መጣች።
ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሚድዋይፈሪ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። ከዚያ በፊት “ፕሬይዝ” የተሰኘ የግል ተቋም ውስጥ በህፃናት መምህርነትና እንክብካቤ ዙሪያ ስልጠና በመውሰድ ለስራዋ ብቁ ሆናለች። በመቀጠልም ከሃዋሳ ኢንፎሊንክ ኮሌጅ በ2010 ዓ.ም በአካውንቲንግ ተመርቃለች።
ህፃናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲወዱ ከሚያደርጓደቸው ተግባራት ቀዳሚዎቹ ምንድናቸው ብለን ላነሳንላት ጥያቄም የሚከተለውን ምላሽ ሰጥታናለች፦
“ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲወዱ አብረዋቸው ያሉ መምህራን እውነተኛ ፍቅር መስጠት፣ ልጆችን በሚሰሩት ስራ ማበረታታትና ማድነቅ፣ ለመንከባከብ መዘጋጀት፣ ስህተታቸውን አለማጉላት፣ ከሌሎች ጋር አለማወዳደር፣ ሲያጠፉ አለመቆጣት፣ አሉታዊ ቃላትን አለመጠቀም በተቃራኒው እችላለሁ ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉ ቃላትን መጠቀም ያስፈልጋል” ስትል ትናገራለች።
“እንደ ተቋም ደግሞ በተለይ በመዋዕለ-ህፃናት ደረጃ የሚሰሩ አካላት ስዕላዊና ማራኪ መርጃ መሳሪያ ቢጠቀሙ መልካም ነው። እኔ አሁን የምሰራበት እናት ማውንት ኦሊቭ ትምህርት ቤት ሞንቶሶሮ የማስተማሪያ መመሪያ ነው የሚከተለው።
“በዚህ መመሪያ መሰረት ልጆች እያዩ፣ እየሰሩ፣ እየዳሰሱና እየተጫወቱ እንዲማሩ ነው የሚደረገው። ያም ልጆች ትምህርታቸውን እንዲወዱ ከማድረጉም በላይ ነገሮችን በቀላሉ እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡
“ከዚህም በተጨማሪ ልጆች ትምህርታቸውን እንዲወዱ ወላጆችና መምህራን በጋራ ሊሰሩ ይገባል። በተለይም በቤት ውስጥ ሲሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን በንቃት ሊከታተሉ ይገባል። ከትምህርት ቤት መልስ በየቀኑ ምን እንደተማሩ ማወቅና መርዳት አለባቸው።
“ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመን ተግዳሮት አብዛኛው ወላጆች ልጆቻቸውን በተለይ በአፀደ ህፃናት ደረጃ ያሉ ልጆቻቸውን ሲልኩ ትምህርት የሚሰጥ አይመስላቸውም። ስለዚህ ልጆቹን አይረዷቸውም፤ ልጆቹን የሚልኳቸው እንዲውሉ ብቻ ነው።
“በዚህም የተነሳ ምንም ዓይነት ክትትል አያደርጉም። በተለይ አንዳንዶች በስራ ምክንያት ጠዋት ወጥተው ማታ የሚገቡ ወላጆች አሉ። ስለዚህ ልጆቹ ከወላጆቻቸው በቂ ጊዜና ክትትል ስለማይደረግላቸው ለስነ-ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ይዳረጋሉ።
“ትምህርት ቤት ሲመጡም እንደሌሎቹ ልጆች ደስተኛ አይሆኑም። እኛም እንደመምህር ልጆቹን ለመረዳትም ሆነ ለመርዳት እንቸገራለን። በተለይም ልጆች በቤት ውስጥ አዘውትረው የሚያከናውኑት ተግባር ወይም መስራት የሚወዱት ነገር ካለ ወላጆች አስተውለው ለመምህራን ስለማያሳውቁ እንቸገራለን።
“አንዳንድ ልጆች ስዕል መሳል ይወዳሉ፥ አንዳንዶች ደግሞ ጨዋታዎችን በጣም ሊወዱ ይችላሉ፤ ያንን የልጆቹን ፍላጎት ወላጆች ለመምህራኖች በግልፅ ቢያሳውቁ ልጆቹ የበለጠ ውጤታማ መሆን ይችላሉ። ስለዚህ የግልፅነት አለመኖር ችግሮቹ ይበልጥ እንዲስፋፉ ወይም በቀላሉ መፍትሔ እንዳያገኙ ሲያደርግ እንመለከታለን” በማለት ነበር በስራ ላይ የታዘበችውን ያጋራችን።
በመጨረሻም በተለያየ ጊዜ የታዘበቻቸው ክፍተቶች እንዲቀረፉ ያለችውን ሃሳቧን እንዲህ በማለት ትቀጥላለች፦
“የትምህርት ስራ የጋራ በመሆኑ ሁሉም ለዘርፉ ትኩረት ማድረግ አለበት። የመንግስትም ሆነ የግል የትምህርት ተቋማት ለመምህራን ልዩ ትኩረት ቢሰጡ መልካም ነው። መምህራን ከትምህርት ጋር የተያያዘ ስልጠና የሚያገኙበት እና ብቁ የሚሆኑበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ይሆናል። በተለይም ወላጆች ብቁ ትውልድ እንዲፈጠር ልጆቻቸውን መከታተልና ከመምህራን ጋር አብረው መስራት አለባቸው፡፡
“በወላጆች ወይም አሳዳጊዎች፣ ቤተሰቦች እና አስተማሪዎች መካከል ጠንካራ አጋርነት ሲኖር በተማሪዎች ላይ የተሻለ ውጤት ይገኛል። እንደ ሀገርም በዘርፉ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ትልቅ ድርሻ ስለሚኖረው ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
“የአፀደ ህፃናት መምህራን ልጆች በጨዋታ እንዲማሩ ያበረታታሉ። አካላዊና ንግግራዊ ተግባራት እንዲያከናውኑ፣ ስዕል እንዲስሉ፣ መዝሙር እንዲዘምሩ፣ በአሻንጉሊት እንዲጫወቱ እና የተለያዩ መጽሃፍት እንዲያነቡ ያደርጋሉ። ልጆች ከሌሎች ጋር በመተባበር መጫወቻዎችን መጋራት መልመዳቸው እና ተራ በተራ መጫወታቸው ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ እና ግንኙነታቸውን እንዲያጠነክሩ ይረዳቸዋል።
“ልጆች በዚህ ዕድሜያቸው መደበኛ ቋንቋን እንዴት እንደሚናገሩ እና እንደሚረዱ ጨምሮ ስለ ድምጾች፣ ቃላት እና ዓረፍተ ነገር ይማራሉ። ለዚህ ሁሉ ስኬት ትልቁን ድርሻ የሚወጡት መምህራን ናቸው።”
በስራ ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች የሚመሰክሩላት መምህርት ለምለም ዳንኤል በ2011 ዓ.ም ወደ ትዳር የገባች ሲሆን፤ የአንድ ልጅ እናትም ሆናለች።
የትምህርት ተቋማት እና በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው የሚለውን የመምህርት ለምለም ንግግርን እኛም ተጋርተነዋል። ሰላም!
More Stories
ለሆስፒታሉ የተበረከቱ የህክምና ቁሳቁሶች ለአገልግሎት ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የቦንጋ ገብረጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ባለሙያዎች ተናገሩ
የመንግሥት ሠራተኞች ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ቡናን በዘመናዊ መንገድ በማልማታቸዉ በተተከለ አንድ አመት ጊዜ ዉስጥ ማፍራት መጀመሩን በሸካ ዞን የኪ ወረዳ የአላሞ ቀበሌ ወጣት ሞደል አርሶ አደሮች ተናገሩ