የተለያዩ የህክምና መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ

በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ላይ ዞኑ የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲዎችን በማቋቋም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ ገልጿል።

‎በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሚዛን አማን ከተማ ማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ላይ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ወ/ሮ አማረች ሀይሌ እና ወጣት ይሁኔ ተስፋዬ፤ በግል ፋርማሲዎች ላይ ያለውን የመድሀኒት ውድነትን ከማረጋጋት ባለፈ የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ጥራቱን የጠበቀ መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

‎አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲው ከግል ፋርማሲዎች በጥራትም በዋጋም ከ50 እስከ 100 በመቶ የዋጋ ልዩነት መኖሩን ገልፀው፤ በቀጣይም አንዳንድ የወባና የመሳሰሉ ሌሎች መድሀኒቶች እንዲሟሉ ጠይቀዋል።

‎የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ባለሙያና አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ ስንታየሁ፤ ከወባ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ በፋርማሲው የወባ ኳርተም እና አርቱሱኔት ፍላጎት መኖሩን ገልጸው በፋርማሲው እንዲሟላ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።

‎የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሄኖክ አባጅፍር በጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የመድሀኒት እጥረትን ለመቅረፍ የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ መቋቋሙ አጋዥ እንደሆነ ተናግረው፤ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ህበረሰቡን ካልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለመታደግ ትልቅ ፍይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

‎በዚህም በዞኑ ሰባት መዋቅሮች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ መምሪያው እየሰራ መሆኑን ተናግረው፤ ቀድመው የመድሀኒት መደብር ግንባታ አጠናቀው ወደ አገልግሎት የገቡ ሚዛን አማን እና ሸኮ ወረዳ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ገልፀዋል።

‎ቀሪ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በግንባታና ከፊሉ በኪራይ ቤቶች ላይ አገልግሎቱን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የመድሀኒት ግዢ ሂደት ላይ መሆናቸውን አቶ ሄኖክ ተናግረዋል።

‎ዞኑ ባለፈው 2017 በጀት ዓመት በወባ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ የተፈተነበት ሂደት መኖሩን ያወሱት አቶ ሄኖክ፤ ይህንን ለመቀነስ በዘንድሮ 2018 ማከም እና መከላከል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

‎በዚህም በዞኑ ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ ጫና ያለባቸውን ወረዳዎችንና ከተማ አስተዳደሮችን በመለየት የአጎበር ስርጭት እና የኬሚካል ርጭት እንዲሁም የቅድመ መከላከል ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

‎በ2018 በጀት ዓመት የመድሀኒት እጥረትን ለመቅረፍ አጠቃላይ 35 የጤና መዋቅሮች እና ማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲን ጨምሮ 130 ሚሊየን ብር መድሀኒት ግዢ ለመፈጸም ከጅማ መድሀኒት አቅራቢ ድርጅት ውል መግባቱን አቶ ሄኖክ ገልፀው፤ ይህ ተፈፃሚ ሲሆን አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ይቀረፋሉ ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ዮናስ ወ/ገብርኤል – ከሚዛን ጣቢያችን