የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል የቋንቋና የባህል ሲንፖዚየም እየተካሄደ ነው
ሀዋሳ: መስከረም 21/2018 ዓ.ም ዓ.ም (ደሬቴድ) የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ሄቦ በዓል የቋንቋና የባህል ሲንፖዚየም በሳጃ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የየም ብሔረሰብ የቋንቋና የባህል ሲፖዚየምና የፖናል ዉይይቱ በተለያዩ ባህላዊና ኪነ ጥበባዊ ክዋኔዎች በድምቀት እየተካሄደ ነው።
“ሄቦ” የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል መሆኑን ያመላከቱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ፥ ከጭጋግና ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከአሮጌው ምዕራፍ ወደ አዲሱ ምዕራፍ መሻገሪያ ነው ብለዋል፡፡
የሄቦ በዓል የአዲስ ዓመት ብርሃን ማብሰሪያ፣ በተለያየ ምክንያት ከአካባቢው እርቀው የሚኖሩ ወገኖች ከወላጆቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ታላቅ ክብረ በዓል መሆኑን ጠቁመው፥ መደበኛ የሄቦ በዓል መከበር የሚጀምረው መስከረም 14 ቀን በመሆኑ ይህ ቀን “ካማ-ኬሳ” እንደሚባል አመላክተዋል።
“ካማ” ማለት ማር ሲሆን “ኬሳ” ማለት ደግሞ መውጣት መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፥ ወደ አዲስ አመት ለመግባት ቂምና ቅሬታን በማስወገድ መቀደስን የሚያመላክት ሲሆን ቅራኔና የሰነበተ ቂም በሽማግሌዎች አማካይነት እርቀ ሰላም ወርዶ ቂምና ቁርሾ የሚወገድበት በሀገር ሽማግሌዎች ሥርዓት የሚፈጸምበት ቀን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በዓሉ በሥራ ምክንያት፣ ባለመግባባትም ተለያይቶ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ተቀራርበው ስለአዲሱ ዓመት የሚመካከሩበት፣ የሚተሳሰቡበት፣ የሚያቅዱበት በዓል በመሆኑ ቀጣይ በሚቀርቡ የሲምፖዚየም መነሻ ሃሳቦች ተመካክረን አቅደን የምንወጣበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ይሁን አሰፋ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የመንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ፣ አቶ ዳዊት ኃይሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃና ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም አቶ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የር/መስተዳድሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ በዝግጅቱ ላይ እየተሳተፉ ነው።
በሲንፖዚየሙ ላይ ከተለያዩ አከባቢዎችና ከሦስቱም የዞኑ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የብሔረሰቡ ተወላጆች፣ ባለሀብቶች፣ የትምህርት አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸዉ ባለድርሻ አካላት እየሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
የተለያዩ የህክምና መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ
የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት በሣጃ ከተማ እየተከበረ ነው
በክረምት ወራት የታየውን ትጋት በበጋውም ለመድገም ቁርጠኞች መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ