በኦሞ ወንዝ ሙላት ከተፈናቀሉት ባሻገር ስጋት ውስጥ የወደቁ አርብቶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

በኦሞ ወንዝ ሙላት ከተፈናቀሉት ባሻገር ስጋት ውስጥ የወደቁ አርብቶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በወረዳው ለተፈናቀሉና በአደጋ ስጋት ውስጥ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች ድጋፍ ማድረጉም ተመላክቷል።

ከወንዙ ሙላት ባሻገር የፍሰት አቅጣጫ መቀየርን ተከትሎ በርካታ ቀበሌያት የግጦሽ ቦታዎች በውሃ የተሸፈኑ ሲሆን የመኖሪያ መንደሮችም ከፍተኛ የአደጋ ስጋት አጥልቶባቸዋል።

እነዚህን ዜጎች ከተጋረጠባቸው አደጋ ለመከላከል ከመንግስት የተለያዩ ጥረቶች ጎን ለጎን በአጋር ድርጅቶችም ድጋፍ ሲደረግላቸዉ ቆይቷል።

በመሆኑም ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለተጎጂዎቹ የተለያዩ የእለት ደራሽ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን ድጋፍ ማቅረቡን አስታውቋል።

የድርጅቱ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ እሸቴ ተሾመ እንደገለጹት፤ ድጋፉ በዋናነት የተፈናቀሉና በአደጋ ስጋት ውስጥ የሚገኙ 1750 አርብቶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያለመ ሲሆን በድጋፉ የውሃ ጀሪካኖች፣ ባሊዎች፣ የገላና የልብስ ሳሙናዎችን ጨምሮ የማጠቢያ ባዞችና ሌሎች የቤት ውስጥ መገልገያዎች የቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዕለት ደራሽና የመገልገያ ግብዓቶችን ባካተተው ድጋፍ፤ 48 ኩንታል ሩዝ፣ 52 ጀሪካን ፈሳሽ ሳሙና፣ 60 ጥንድ አንሶላዎች፣ 50 ብርድ ልብሶች፣ 20 የማብሰያ ቁሳቁሶች እንዲሁም 34 ጥቅልል ምንጣፎችና 69 የፕላስቲክ ጠረጴዛዎች ይገኙበታል ያሉት ማናጀሩ፤ ለዚህም ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን አስረድተዋል።

የድርጅቱ ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የወንዙ ሙላት ባስከተለው ጉዳት ለአደጋ የተዳረጉ ዜጎችን ለማቋቋም መንግስት የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርግም ገና ብዙ አቅም የሚጠይቁ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህን ከግምት በማስገባት ወርልድ ቪዥን ያሳየው አጋርነት የሚደነቅ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዳሠነች ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ግርማ ናቸው።

የወረዳውን የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት ድርጅቱ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ድጋፉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት መሳለጥ አይነተኛ ሚና ያለው በመሆኑ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

እንደ ወቅታዊ መረጃዎች አካባቢው የከፋ የአደጋ ስጋት የተጋረጠበት በመሆኑ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ የተጀመሩ ጥረቶች አፋጣኝና የተቀናጀ ርብርብ የሚጠይቁ መሆናቸውን የወረዳው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኦስማን ሰይድ ያብራራሉ።

ስለሆነም የወረዳውን ህዝብ ከገጠመው የህልውና አደጋ ለመታደግ ሌሎች ድጅቶችም የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቅርቡ ወደ ስፍራው ያቀናው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የተመራ ከፍተኛ የክልሉ የመንግስት አመራሮችም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ዘገባው የጂንካ ቅርንጫፍ ጣቢያችን ነው