የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት ላይ ያሉ አሉታዊ አመለካከቶችን በመቅረፍ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት ላይ ያሉ አሉታዊ አመለካከቶችን በመቅረፍ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

ሚኒስቴሩ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር “መሰናክሎች ማስወገድ፣ አቅምን መገንባት፣ የቤተሰብ አቅድ አገልግሎት ተደራሽ ለሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች” በሚል መሪ ቃል አለም አቀፍ የቤተሰብ እቅድ ቀን በወልቂጤ ከተማ አክብሯል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ፣ በሃገራችን ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ የተከበረው የቤተሰብ አቅድ ቀን በወልቂጤ ከተማ በተከበረበት ወቅት የተገኙት በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህጻናት የአፍላ ወጣቶች ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ማራያማዊት አስፋው፤ የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚ መሆን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሃገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም አሁንም ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ከመሆኑም ባለፈ ይህን መተግበር ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት ላይ ያሉ አሉታዊ አመለካከቶችን በመቅረፍ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል አበክሮ መስራት እንደሚገባና በተለይም በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ተወካይና የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀላፊ አቶ ማሙሽ ሁሴን፤ ክልሉ የጤናውን ዘርፍ ስርአት እንለውጥ የሚል አላማ በማንገብ የጤና ኤኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አቅምን በማጎልበት በዘርፉ በሃገር አቀፍ ዳረጃ ሞዴል የሆኑ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት አመት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ እናቶች የቤተሰብ እቅድ መጠቀማቸውን ገልጸው፤ ከክልሉ ካለው የህዝብ ምጣኔ አንጻር ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

ይህም ሴቶች እፎይታ አግኝተው ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችለውን የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ይበልጥ ለማስፋት ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚደረግና ለውጤቱም በየደረጃው ያለ አካል ተሳትፎውን ማጠናከር ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ ወረርሽኞችን ከመከላከል ጀምሮ በቤተሰብ እቅድ ላይ ውጤት ተመዝግቧል።

የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በመጠቀሙ ረገድ የተሻሉ ስራዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ከግብአት አቅርቦት ጋር አሁንም ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የወልቂጤ ጤና ጣቢያ አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ በተሳታፊዎች ጉብኝት ተደርጓል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን