የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለፀ
በዞኑ የአማርድ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ዙር የተቀበላቸውን ተማሪዎች ትምህርት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኗል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአዳሪ ትምህርት ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ላጫ ጋሩማ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፋት መልዕክት እንዳሉት፤ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
አማርድ አካዳሚ ከዞኑ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡና የአካዳሚውን የመግቢያ ፈተና ያለፉ 120 ተማሪዎችን ተቀብሎ ትላንት የመማር ማስተማር ተግባሩን ጀምሯል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዳሪ ትምህርት ቤት ያልነበረው ብቸኛው ዞን ጉራጌ ዞን እንደነበረ የጠቀሱት አቶ ላጫ፤ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከጉራጌ ወዳጆችና ተወላጆች ጋር በቅንጅት በተደረገው ርብርብ እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ለግንባታው ከፍተኛ በጀትና ትኩረት በመሰጠቱ እውን እንደሆነ በመጠቆም ለዚህ ስኬት ኮንትራክተሩንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ በ120 ተማሪዎች ስራውን ይጀምር እንጂ እስከ 960 ተማሪዎች ማስተናገድ የሚችሉ የመማሪያ ክፍሎች እንዲሁም 460 የተማሪ ማደሪያዎች አሉት ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የተማሪዎችን ቁጥር እያሳደገ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።
ትምህርት ቤቱ ደረጃውን እንዲጠብቅ እና ግንባታው ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
የተቋሙ ዓላማ ተማሪዎቹን የዛሬ አራት አመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች መቶ መቶ ማምጣት እንዲችሉና በሃገሪቷ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ጭምር እንደሚሰራ ጠቁመዋል ዋና አስተዳዳሪው።
የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ የዞኑ ህዝብ የበርካታ አመታት ጥያቄ የነበረው አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ስራ የጀመረው በዞኑ አስተዳደር፣ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ፣ በልበ ቀና ባለሀብቶችና በመላዉ የጉራጌ ህዝብ ትብብር መሆኑን በመግለፅ፤ በቀጣይ አካዳሚው ውጤታማ እንዲሆንና በመማር ማስተማሩ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
የጉራጌ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት በመገንባትና የትምህርት ቁሳቁስ በማቅረብ ረገድ የረጅም ጊዜ ታሪክ እንዳለው ተናግረው፤ ይሁን እንጂ ለተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ተወዳዳሪ ትውልድ ከመቅረጽ አንጻር የተፈጠረውን ክፍተት ለመቅረፍ በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች አዳሪ ትምህርት ቤቱ ገብተው የመማር አቅም ያላቸው ተማሪዎች መፍጠር ትልቅ ስራ የሚጠይቅ እንደሆነም አመላክተዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም የህዝቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረው አዳሪ ትምህርት ቤት ስራ መጀመር በዞኑ የሚገኙ ጎበዝ ተማሪዎች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ የተሻለ ክህሎት ባላቸው መምህራን እንዲሁም ግብአት፣ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት እርስ በርሳቸው እንዲፎካከሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
በዛሬው እለት የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው አማርድ አካዳሚ በአለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተጽዕኖ ፈጣሪ ተማሪዎች የሚፈሩበት ተቋም ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዘንድሮ ዓመት 120 ተማሪዎችን በመቀበል ስራ መጀመሩን የተናገሩት አቶ መብራቴ፤ በቀጣይ አካዳሚው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ 960 ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ተናግረዋል።
የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ስራ መጀመር በወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች መካከል ከፍተኛ የውድድር መንፈስ የሚፈጥር መሆኑም አመላክተዋል።
ተማሪዎቹ ለትምህርት የሚያስፈልጓቸው የትምህርት ግብዓቶች ተሟልቶላቸው ሙሉ ጊዜያቸውን ትምህርት ላይ በማተኮር ተወዳዳሪ ዜጎች እንዲሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እና ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል።
ተማሪ ጸበሉ ሳህሌ እና ተማሪ ኢምራን አብድልሀኪም አዳሪ ትምህርት ቤት በመግባታቸው በጣም ደስተኛ እንደሆኑና ግቢው ለንባብ ምቹ በመሆኑ የወደፊት አላማቸውን ለማሳካት የሚያግዛቸው በመሆኑ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚተጉ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የተለያዩ የህክምና መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ
የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት በሣጃ ከተማ እየተከበረ ነው
በክረምት ወራት የታየውን ትጋት በበጋውም ለመድገም ቁርጠኞች መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ