“የማሽቃሬ ባሮ” በዓል እሴቶች ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና መሰረት መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ
የሸካቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነው “ማሽቃሬ ባሮ” በዓል የይቅርታ፣ የእርቅና የአንድነት እሴቶቹ ለክልሉ ሰላምና ዘላቂ ብልጽግና ወሳኝ መሰረት መሆናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለመላው የሸካቾ ብሔረሰብና ወዳጆች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ማሽቃሬ ባሮ አዲስ ዓመትን ከመቀበል የዘለለ ጥልቅ ማህበራዊና ባህላዊ ትርጉም ያለው ውድ ቅርስ መሆኑን አስምረውበታል።
በመልዕክታቸውም “ማሽቃሬ ባሮ ቂምና በቀል የሚረሳበት፣ የይቅርታና የእርቅ መንፈስ የሚሰፍንበት፣ ፍቅርና መተሳሰብ የሚነግስበት ልዩ ወቅት ነው” ያሉት ዶ/ር ነጋሽ፤ የበዓሉ እውነተኛ ትርጉም ከሰው፣ ከፈጣሪና ከተፈጥሮ ጋር ሰላምን በማደስ ወደ አዲሱ ዓመት በንጹህ ልብ መሸጋገር እንደሆነ አብራርተዋል።
የሸካ ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የብዝሃ ህይወት ቀጠናን ጨምሮ በልምላሜና በሀብት የተሸለመ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ “የዚህ ዉብ መልክዓ ምድርና የተፈጥሮ ሀብት ዋልታና ጠባቂ የሆነው ደግሞ እንደ ማሽቃሬ ባሮ ያሉ ህዝባዊ እሴቶቻችን ናቸው” ብለዋል።
በዓሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፈው ተፈጥሮን የመንከከባከብ ባህል ለክልሉ ውበትና ዘላቂነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን የይቅርታና የአብሮነት መንፈስ በበዓሉ ወቅት ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ህይወቱ ውስጥ በማስረጽ፣ የክልሉን የሰላም፣ የልማትና የጋራ ብልጽግና ግቦች ለማሳካት በጋራ እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።
“የበዓሉን መንፈስ በመያዝ፣ ከፋፋይና ኋላቀር አስተሳሰቦችን በመዋጋት ለክልላችንና ለሀገራችን እድገት በጋራ እንቁም” ሲሉ ማሳሰባቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።
በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱ የሸካቾ አዲስ ዓመት ለመላው የብሔረሰቡ አባላትና የክልሉ ህዝቦች የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤናና የተትረፈረፈ በረከት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
More Stories
የተለያዩ የህክምና መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ
የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት በሣጃ ከተማ እየተከበረ ነው
በክረምት ወራት የታየውን ትጋት በበጋውም ለመድገም ቁርጠኞች መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ