ለትምህርት ዘመኑ የትምህርት ዘርፍ ስራዎች ውጤታማነትና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ለትምህርት ዘመኑ የትምህርት ዘርፍ ስራዎች ውጤታማነትና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ወቅቱ በየደረጃው ባሉ የትምህርት ዕርከኖች የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ስራ ጅማሮ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፤ ለትምህርት ዘመኑ የትምህርት ስራዎች ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ የትምህርት ጥራትን የማሻሻል፣ ትውልድን በተሻለ መሠረት ላይ የማነፅ እና ለተሻለ ውጤት የማብቃት የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ራዕይ ለሰነቀ ሀገር እና መንግስት የትምህርት ዘርፍ ውጤታማነትን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች ትምህርት ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ባለፉ ጊዜያት እንደ ሀገር ያጋጠመን የትምህርት ስብራት ለማከም በህብረተሰቡ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በተከናወኑ የትምህርት ተደራሽነትን የማሳደግ እና የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡
ትምህርት በበቂ ዕውቀትና ክህሎት የተገነቡና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጹ የዛሬ ሀገር ገንቢዎችንና የነገ ሀገር ተረካቢዎችን በማፍራት ጠንካራ ሀገር ለትውልድ የማሻገር ታላቅ ተግባር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዘርፉ ውጤታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የህብረተሰቡ የትምህርት ልማት ተሳትፎ በተለይም ትምህርት ቤቶችን በመጽሐፍትና ሌሎች ግብዓቶች የማጠናከር፣ የማደስና አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ በተያዘው የ2018 የትምህርት ዘመንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለተማሪዎች ውጤታማነት ማደግ እና የትምህርት ጥራት መረጋገጥ የግብዓት መሟላት ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህ ረገድ በክልላዊ የአንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ኢንሼቲቪ እና በሀገራዊው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የተገኙ ስኬቶች ተሞክሮን ቀምሮ ማላቅ ይገባል ብለዋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ በቀዳሚነት የተማሪ ወላጆች፣ መምህራን እና በየደረጃው ያለው የትምህርት ዘርፍ አመራር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ከወዲሁ ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በተለይ የተሟላ ዕውቀትና ክህሎት ያለው፣ መልካም ስነ-ምግባርና ስብዕናን የተላበሰ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው የቀለም አባት የሆኑት መምህራን የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እንደተለመደው ከምንም በላይ ቅድሚያ ለትውልዱ በመስጠት በትጋት እንዲሰሩ ከአደራ ጭምር ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ ለተማሪዎች ውጤታማነት ማደግና በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ለማድረግ ከሚከናወኑ በርካታ ስራዎች መካከል ከ873 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተደራሽ ያደረገ የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር አንዱ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በትምህርት ዘመኑ ለታለመው የማህበረሰብ አቀፍ የምገባ ፕሮግራም ስኬት በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
More Stories
የተለያዩ የህክምና መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ
የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት በሣጃ ከተማ እየተከበረ ነው
በክረምት ወራት የታየውን ትጋት በበጋውም ለመድገም ቁርጠኞች መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ