በጎፋ ዞን ላሃ ከተማ አስተዳደር በ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ኮብልስቶን ንጣፍ ስራ መከናወኑ ተገለጸ

በጎፋ ዞን ላሃ ከተማ አስተዳደር በ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ኮብልስቶን ንጣፍ ስራ መከናወኑ ተገለጸ

በህብረተሰብ ተሳትፎ 4 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ጥገና ስራ መከናወኑንም የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የላሃ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ኢያሱ ማሩፋ በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታይ የለውጥ ስራ መሰራቱን ተናግረው፤ ለዚህም የህብረተሰቡ የመልማት ፍላጎትና ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም በ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር 290 ሜትር ኮብልስቶን ንጣፍ መሰራቱን ገልጸው፤ 4 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ጥገና ስራ በህብረተሰብ ተሳትፎ መሰራቱን ተናግረዋል።

በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 14 ክፍል ያለው ቢሮ እና መለስተኛ አዳራሽ ያለበት የማዘጋጃ ቤት ህንፃ በ8 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር እየተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከተማው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ የከንቲባ ህንፃ፣ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የፍርድ ቤትና የፍትህ ተቋማት፣ ግንባታዎች መጀመራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ቡራቃ አሊዬ አብራርተዋል።

የላሃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሸናፊ ጮራ የከተማዋን ደረጃ ለማሻሻል በርካታ የመሠረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው በቀጣይ የከተማውን ስትራቴጂክ ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አክለውም ፕላኑ ተግባራዊ ሲደረግ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለሆቴል እና ለሌሎች መሰረተ ልማት ስራዎች መሬት ለማዘጋጀትና ለማቅረብ ወሳኝ መሆኑን አስረድተው በልማት ስራ ላይ የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከላሃ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አለሙ ኤሬታ እና ወይዘሮ አሰገደች አርሰኖ፤ ላሃ ከተማ ከተመሠረተች አጭር ጊዜ ቢሆንም የመሰረተ ልማት ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንደሚገኝ ተናግረው መንግስት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ: ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን