ህሙማንን የመጠየቅና የመርዳት ባህል ሊዳብር እንደሚገባ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ገለፀ

ህሙማንን የመጠየቅና የመርዳት ባህል ሊዳብር እንደሚገባ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ገለፀ

‎የከተማው ፖሊስ በሆስፒታሉ የሚገኙ ህሙማንን በመጠየቅ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስና ሌሎች ግብአቶችን ድጋፍ አድርጓል።

‎የአርባ ምንጭ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ጥሩነሽ ተስፋዬ፤ የታመመን መጠየቅ፣ የተቸገረን መርዳት ከህሊና እርካታ ባለፈ በፈጣሪ ዘንድ ተወዳጅ ተግባር በመሆኑ የአብሮትና የመረዳዳት ልምዳችን ሊዳብር ይገባል ብለዋል።

‎የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል እንዳሉት፤ የፖሊስ አባላቱን በማስተባበር ከከተማው ህብረተሰብ ከተሰበሰበ ድጋፍ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የታመሙ ወገኖችን በመጎብኘት የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና ሌሎች ግብአቶችን ማበርከት ተችሏል።

‎የከተማው ፖሊስ ሰላምን ከማስጠበቅ ባሻገር በሚያደርገው ማህበራዊ እንቅስቃሴ የህሊና እርካታ የሚያገኝበት በመሆኑ የሚደረጉ በጎ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኮማንደሩ አረጋግጠዋል።

‎የከተማው ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ፃራ የፀጥታ መዋቅሩ ጉዳት የደረሰባቸውን አባላት ሲጎበኝ መቆየቱን ገልፀው፤ ህሙማንን መጠየቅ ደግሞ በህብረተሰቡ ዘንድ አክብሮነት የሚያስገኝ ስለሆነ ሌሎች ተቋማትም ከዚህ ልምድ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።

‎የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አምባቸው ዱምአ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ የሚገኙ ህሙማንን በሀይማኖት ተቋም፣ በቡድን ብሎም በግል የመጠየቅ ባህል የተለመደ ቢሆንም በተቋም ደረጃ አባላትን አስተባብሮ ለህሙማኑ ድጋፍ በመደረጉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

‎ከምንም በላይ የህሊና እርካታ የሚሰጥ በጎ ተግባር የፈፀሙ የከተማው ፖሊስ አባላት ላበረከቱት አስተዋፅኦ በህሙማኑና በሆስፒታሉ ስም አመስግነዋል።

‎በሆስፒታሉ ተኝተው ህክምና የሚደረግላቸው ታካሚዎች በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀው የመጠያየቅና የመተባበር ባህላችን ሊዳብር ይገባል ብለዋል።

‎ዘጋቢ፡ ገነት መኮንንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን