የመስቀል ወፍና መስቀል

‎የመስቀል ወፍ ለወራት ጠፍታ ቆይታ አዲስ ዓመት ሲገባ በተለይ ደግሞ መስከረም ሲጋመስ እንደምትከሰት በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።

አደይ አበባ ከመስቀል ወፍ ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለ ይህም አደይ አበባም መስከረም ወርን ጠብቆ መምጣቱ ነው።

‎በአባባልም አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ ጠፍቶ ቆይቶ ድንገት ሲከሰት ‘ ምነው የመስቀል ወፍ ሆንክ’ ይባላል። ይህም ለረጅም ጊዜ ሳይታዩ ወይም ጠፍቶ ቆይቶ መታየትን ለማመልከት ማህበረሰቡ በተለምዶ  የሚጠቀምበት አባባል ነው።

ቀለማቸውና ዝማሬያቸው ከአዲስ ዓመትና ከመስከረም የፀሐይ ወቅት ጋር ተዳምሮ ከሚፈጠረው መልካም ስሜት ጋር የሁሉንም ቀልብ ስለሚስቡ ሁሉም ይመለከታቸዋል ሁሉም አዲስ ወፍ የመስቀል ወቅትን ጠብቆ እንደመጣ ይታመናል።

‎የመስቀል ወፍ ተብለው የሚጠሩት አእዋፋት በስፋት ታይተው በበርካቶች ዓይን ውስጥ የሚገቡት የክረምቱ ወራት አብቅቶ የበጋው ወቅት በሚጀምርበት ጊዜ በማየታችን እነዚህን አባባሎች እንድንጠቀም አድረጎናል፡፡

‎አእዋፋቱ አዲስ የሚሆኑብን አብረውን በዙሪያችን በሚቆዩበት ጊዜ የሚኖራቸው ገጽታ በመስከረም ወር ላይ በተፈጥሯዊ ሂደት ቀለማቸው ተለውጦ አይነ ግቡ ስለሚሆኑ የዚያ ወቅት አዲስ ክስተት እንደሆኑ ስለሚታሰብ ነው።

‎የመስቀል ወፍ ተብለው የሚታወቁት አእዋፋት እንደሚባሉት ለረጅም ጊዜ ተሰውረው ቆይተው በመስቀል ሰሞን የሚከሰቱ ሳይሆኑ ዘወትር አብረውን የሚኖሩ ሲሆኑ የመስቀል ወፍ በዝማሬዋ ማራኪ እና የስነፍጥረት ድንቅ ወፍ እንደሆነች ሊቃውንት ይመሰክራሉ።

‎እንደባለሙያዎች ጥናት  ከሆነ በኢትዮጵያ በመስቀል ወፍ ስም የምትታወቀው አንድ አይነት ዝርያ ያላት ወፍ ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸው ከአራት በላይ የሆኑ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው አእዋፋት እንደሆኑ ይገራል።

‎ለዚህም እንደምሳሌ የሚጠቅሱት ቁራ በሚል የሚጠሩ አእዋፋት ቢኖሩም በውስጣቸው የተለያዩ ዝርያዎች እንዳሉት ሁሉ የመስቀል ወፍ ውስጥም የተለያዩ የወፍ አይነቶች መኖራቸውን ነው።

‎ከእነዚህ የመስቀል ወፎች መካከልም አዘውትረን የምናያቸው በቅርብ የምናውቃቸው ትንንሽዬዎቹና ድንቢጥ ተብለው የሚታወቁት አእዋፋትም በመስቀል ወፍነት ከሚጠሩት ውስጥ ይካተታሉ።

‎እንደየቋንቋውና እንደየአካባቢው እነዚህ ወፎች የየራሳቸው ስያሜና መጠሪያ ሊኖራቸው እንደሚችል እንዲሁም ወፍ የሚለው ግን በርካታ አይነት ወፎች በውስጡ ያካትታል፡፡

‎አእዋፋቱ በአብዛኛው ዘር በል በመሆናቸው በዚህ ወቅት ደግሞ የሚደርሱ ሰብሎች በስፋት የሚገኙበትና ወፎቹም የሚራቡበት አመቺ ወቅት በመሆኑ በስፋት ይታያሉ፡፡

‎እነዚህ አእዋፋት ባሕሪያቸው ከአንድ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ ወቅቶችንና የአየር ሁኔታዎችን እየተከተሉ የሚሰደዱ በመሆናቸው በሌሎች ሃገራት ውስጥም ይገኛሉ።

‎የተለያዩ አእዋፋት በተለያዩ ወቅቶች በተለይ ከሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ወደ አፍሪካ የሚመጡ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ ወደዚያው የሚሄዱም አሉ።

‌‎

‎የመስቀል ወፍ ተብለው የሚታወቁት አብዛኞቹ ግን በኢትዮጵያ ውስጥና በዙሪያዋ ባሉ ሃገራት ውስጥም እንደሚገኙ ይነገራል። ስለዚህ አእዋፋቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያ፣ በኡጋንዳና በታንዛንያ ውስጥ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ።

‎በልምድ እንደምንለው የመስቀል ወፍ ለረጅም ጊዜ ጠፍተው ቆይተው በመስቀል ወቅት የሚከሰቱ እንዳልሆኑና በዙሪያችን አብረውን የሚኖሩ ናቸው።

‎”ለዚህም የአዕዋፋቱን ተፈጥሮ መረዳት ያስፈልጋል” እነዚህ ወፎች ላይ ይህ ተፈጥሯዊ ለውጥ የሚታየው በዋናነት በመስከረም ወር ላይ የሚራቡበት ጊዜ በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ከመስቀል በዓል ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ የተለየ ገጽታን ተላብሰው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል።

‎በመስከረም ወር ላይ እንስት አእዋፋቱ እንቁላል ለመጣል የሚዘጋጁበት በመሆኑ ተባዕቱ ለእሱና ለተጣማሪው እንዲሁም ለሚፈለፈሉት አእዋፋት የሚያስፈልገውን ምግብና መጠለያን በሚያገኝበት ቦታ ላይ አንድ የተወሰነ አካባቢን ከልሎ ይይዛል።

‎የመራቢያ ጊዜ በመሆኑ ወንዱ ይህንን በሚያደርግበት ወቅት የላባው መጠን ይረዝማል ቀለሙም ይቀየራል። ቀለሙ ደማቅና ውብ ስለሚሆን የሰዎችን አይን በመሳብ እንደ አዲስ ወፍ ሊታይ ይችላል ይላሉ አቶ ይልማ።

‎ይህ ቀለምም ከሩቅ የሚታይ እንደሚሆን የሚናገሩት ባለሙያው በተለይ ፀሐይ በሚያገኘው ጊዜ በማንጸባረቅ ትኩረት የመሳብ አቅም አለው።

‎በተጨማሪም ለውጡ የሚከሰተው በመራቢያ ጊዜ በመሆኑ እንስት ወፎችን ለመሳብና ለማማለል ከመጥቀሙ በተጨማሪ በአንጸባራቂ ውበቱ በቀላሉ ስለሚታይ፣ እንዲሁም በዚህ ላይ ዝማሬን ስለሚጨምር ሌሎች አእዋፋት የእርሱን አካባቢ እንዲርቁ ያስችለዋል።

‎እንግዲህ ይህ የአእዋፋቱ ሥነ አካላዊ ለውጥ ነው በሌለው ጊዜ በአካባቢያችን ይኖሩ የነበሩትን እነዚህን አእዋፋት ለረጅም ጊዜ ጠፍተው በመስቀል ወቅት ብቅ ያሉ እንዲመስሉ ያደረጋቸው ይላሉ አእዋፋቱን በቅርበት የሚያጠኑት አቶ ይልማ ደለለኝ።

‎ባለሙያው እንደሚሉት በአካባቢያችን ያሉትን አእዋፋት በቅርበት የመከታተል ልምድ ስለሌለንና ክረምቱ አልፎ መስከረም አጋማሽ ላይ አእዋፋቱ ላባቸው በቀለማት አሸብርቆ በቀላሉ አይናችን ውስጥ ሲገቡ በዙሪያችን የነበሩት ወፎች ሳይሆኑ ጊዜ እየጠበቁ ብቅ የሚሉ ይመስሉናል።

‎የመስቀል ወፍ ብለን የምንጠራቸው አእዋፋት ከሌሎች ለየት የሚሉት ተባዕቶቹ በጣም ደማቅ ቀለም ሲኖራቸው፣ ሴቷ ግን ቡኒ ወይም ወደ ግራጫ የሚያደላ ቀለም ነው ያላት፤ በመራቢያ ወቅት ወንዱ ከበርካታ እንስት አእዋፋት ጋር የመሆን ባሕሪ እንዳለውም አቶ ይልማ ይጠቅሳሉ።

‎ስለዚህ የአእዋፋት አጥኚ የሆኑት አቶ ይልማ ደለለኝ እንደሚሉት የመስቀል ወፎች ለረጅም ጊዜ ሳይታዩ ቆይተው መስከረም ወር ላይ የሚከሰቱ ዓመታዊ እንግዶች ሳይሆኑ አብረውን ቆይተው በተፈጥሮ ሂደት የላባቸው ቀለም የሚቀየር ቤተኛ አእዋፋት ናቸው ማለት ነው፡፡

ዘጋቢ፡- በመዝሙረ ዳዊት