ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለደመራ እና መስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ እንኳን ለደመራ እና መስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
መስቀል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት መስዋዕትነት የከፈለበት መንበር በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው እና በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት የሚከበር ደማቅ በዓል ነው፡፡
በዓሉ ምእመኑ የቅዱስ መስቀሉን መገኘት በመዘከር፤ በኅብረት ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት በልበ ብርሃን ተሞልቶ ስለሀገር ሰላምና ስለህዝብ አንድነት ጽሎት በማድረስ ጭምር በልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች በአደባባይ የሚያከብረው፤ የኅብረትና የአንድነት እሴቶች ያሉት ታላቅ በዓል ነወ፡፡
ብርሃነ መስቀሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገርን፣ ከፈተና ወደ ድል መጓዝን ማብሰሪያ ምልክት ሲሆን፤ ደመራው ፈታኙን ወቅት የመሻገራችን ብስራት፤ የመጪው የብሩህ ተስፋ ስንቅ ምልክት ነው፡፡
የዘንድሮውን የመስቀል በዓል የምናከብረው ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን በህዝባችን የተደመረ አቅም በድል አጠናቀን፤ በስኬት ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን በመሸጋገር መፃይ የኢትዮጵያን የንጋት ዘመን በተጨበጠ ብርሃን ተሞልተን ባበሰርንበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡
እንደ ሀገር ተደማሪ አቅማችንን ይዘን መዳረሻችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና በማድረግ በኅብረትና በአንድነት የለኮስነው የዘላቂ ሰላምና ልማት ችቦ ተቀጣጥሎ ብርሃኑን ማየት በጀመርንበት በዚህ ወቅት፤ በዓሉን ስናከብር ከመስቀሉ ታሪክ የተስፋ፤ የጥንካሬና የፅናት ተምሳሌትነት ትምህርት በመውሰድ ሊሆን ይገባል፡፡
የመስቀሉን ብርሃን በልቦናቸው አኑረው ተስፋ ሳይቆርጡ የጸኑ፤ የብርሃነ መስቀሉን መገኘት ለዓለም እንዳበሰሩ ሁሉ፤ ጊዜያዊና ወቅታዊ ችግሮችንና ተለዋዋጭ ፈተናዎች በጽናት በመሻገር በኅብረትና በትብበር ለድል መብቃት እንደምንችል በማሰብ በጋራ ለሰነቅነው የብልጽግና ትልም ስኬት በጽናት መነሳት ይኖርብናል፡፡
መስቀል በእምነቱ አስተምህሮ መሰረት የሰላምና የድኅነት አርማ በመሆኑ፤ በዓሉን አስተምህሮው በሚያዘው መሠረት ፍቅርን በማስቀደም፤ ዕርቅና ይቅርታን በማውረድ እና ሰላምን በማስፈን ማክበር ይገባል፡፡
ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነውና በዓሉን ስናከብር ለጋራ ሰላም በጋራ በመቆምና የአካባቢያችንን ሰላም በማፅናት፤ ያሉንን ፀጋዎች ተጠቅመን ሙሉ አቅማችንንና ትኩረታችንን ልማት ላይ በማዋል የጀመርነውን የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ በመነሳት መሆን ይኖርበታል፡፡
መስቀል ክርስቶስን የምንመለከትበት መስትዋት እንደመሆኑም ብርሃነ መስቀሉን ስናከበር ከትዕቢት ይልቅ ትህትናን ተላብሰን፤ ከመገፋፋት ይልቅ አብሮነትንና አንድነትን አጽንተን፤ ፍቅርንና በጎነትን አንብረን፤ ከራስ በላይ ሌሎች በማሰብ ሰው ተኮር በጎ ተግባራትን የሁልጊዜ ምግባራችን በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡
በዓሉን ስናከብር፤ በየተሰማራንበት መስክ ህዝብንና ሀገርን በታላቅ የአገልጋይነት ስሜት፤ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል የመንፈስ ዝግጅት በማድረግ ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞቴን ለመግለጽ እወዳለሁ!!
ፈጣሪ ሀገራችንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
More Stories
የተለያዩ የህክምና መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ
የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት በሣጃ ከተማ እየተከበረ ነው
በክረምት ወራት የታየውን ትጋት በበጋውም ለመድገም ቁርጠኞች መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ