እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
የመስቀል በዓል ሲታሰብ እውነት ተቀብራ እንደማትቀር እናስባለን። መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ተራራ ሠርቶ ነበር። የቀበሩት ሰዎች ከዚህ በኋላ እንደማይወጣ ደምድመው ነበር። አንዳንድ አማኞችም ተስፋ ቆርጠው ነበር።
ጊዜው በረዘመ ቁጥር ቀባሪዎቹ ያሸነፉ መስሏቸው ተደሰቱ። የተቀበረው መስቀልም ታሪክ የሆነ መሰለ።
ብርቱ ሰዎች፣ እውነት ፈላጊ ሰዎች፣ አቧራውን የሚገልጡ፣ ቆሻሻውን የሚያነሡ ሰዎች፣ ሲመጡ ግን መስቀሉ ከተቀበረበት ወጣ።
እውነት አይቀበርም። ጊዜው ሲደርስ አቧራውን አንሥቶ ዐሻራውን ያሳያል። ሐሰቱን እንደ ጉም አትንኖ፣ ሐቁን እንደ ዐለት አግንኖ ያሳያል።
የኢትዮጵያም እውነት እንደዚሁ ነው። የአውራ ዶሮዎች ጩኸት የፀሐይን መውጣት አያስቀረውም። የሌሊት ወፎች ክንፍ የፀሐይን ንጋት አያግደውም። በዚህም ተባለ በዚያ ፀሐይ ትወጣለች።
የኢትዮጵያ እውነት እንደ መስቀሉ ሁሉ አቧራውን ጥሶ፣ አፈሩን አፍልሶ፣ ቆሻሻውን ደርምሶ ይገለጣል። የወጓት ያዩዋታል። ከላይ ሆነው እንዳዩዋት ሁሉ፣ ከታች ሆነው ይገረሙባታል።
በመደመር ደመራ እየተመራን፣ በትጋት እየቆፈርን፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እናወጣዋለን። ይህ ዓመት የኢትዮጵያ ብርሃን ሲወጣ የምናይበት ይሆናል።
በድጋሚ መልካም የደመራና የመስቀል በዓል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም

More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ እና የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዕቅድ ዙሪያ በታርጫ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው
ኦሞ ባንክ ሳውላ ዲስትሪክት በ2018 በጀት ዓመት ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ቁጠባ ማስመዝገቡን ገለጸ
እየተካሔደ ያለው ሀገራዊ ምክክር በሀገሪቱ አንድነት እና ሠላም ለማስፈን ፋይዳው የጎላ መሆኑን የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ