ደመራ!!
ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን ያስተባበረ መሆኑን ገልጸው የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል
የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ ከጌታችን መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡
ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ የጌታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ብቻ ይሰቀሉበት የነበረው መስቀል ከጌታ ስቅለት በኋላ የመዳን ምልክት እንደሆነ የሀይማኖቱ አስተምህሮ ስረዳል::
ዳሩ ግን ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን በማድረጉ የታወኩ አይሁድ መስቀሉን ከሰዎች እይታ ለመሠወር ወሰኑ:: ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት:: መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል የቆሻሻ መጣያና ማከማቻም አደረጉት:: ምንም እንኳን አይሁድ ለጊዜው መስቀሉን ከዐይን ለመሰወር ቢችሉም ከክርስቲያኖች ልቡና ግን ሊያወጡት አልቻሉም:: የመስቀሉ ብርሃን በልቡናቸው የሚያበራ ክርስቲያኖች እየበዙ መጡ:: መስቀሉንም መፈለግ ጀመሩ::
ንግሥት እሌኒ ልጇን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ክርስትና ሃይማኖትና ስለ ክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡
ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነች፡፡ ንግሥት እሌኒም የተፈጠረውን አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችንን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ/ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡
ንግሥት እሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነፅ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡
ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ/ም ተጠመቀ፡፡ ቅድስት እሌኒም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች እንደደረሰችም ስለ ክብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች፡፡ ቦታውን የሚያስረዳት ግን አላገኘችም፡፡ አይሁድ የተቀበረበትን ቦታ ለማሳየት ባይፈልጉም በኋላ ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመላከታት ዳሩ ግን ኪራኮስ ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከነበሩት ከሦስቱ ተራሮች ውስጥ መስቀሉ የሚገኝበት የትኛው እንደሆነ ለይቶ ማወቅ አልቻለም፡፡
ንግሥት እሌኒ ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ እርዳታ ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠል ጸሎት ተያዘ፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም ጢሱ ሰገደ ብሎታል፡፡
ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡:
መስቀሎቹን ወስደው በሞተ ሰው በተራ ቢያስቀምጡ ጌታችን የተሰቀለበትና በዕለተ ዐርብ ተሰቅሎ የዋለበትና በደሙ መፍሰስ የተቀደሰው መሰቀል የሞተውን ሰው በማስነሣት በሠራው ተአምር ሌሎቹ ሁለቱ ታምራት ባለማድረጋቸው የጌታን መስቀል ለይቶ ማወቅ ተችሏል።
እሌኒና ክርስቲያኖች ሁሉ ለመስቀሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ጊዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡
ንግሥት እሌኒ ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ ከሠራችለት ጊዜ ጀምሮ በመስከረም 17 ቀን አሁን በኢትዮጵያ እንደሚከበረው በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀል ይከበር ነበር።
የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት ስንመለከት በደመራ ዕለት መዘምራን የዋዜማውን ቃለ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፤ ምስባክ ይሰበካል፤ ወንጌል ይነበባል፤ ልዩ ልዩ ያሬዳዊ ሽብሸባዎች ይቀርባሉ፤ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ሰፋ ያሉ ከተሞች ላይ በዓሉን የሚመራ ተረኛ ደብር ይመደባል፤ የተመደበው ደብር ቀደም ብሎ በቂ ዝግጅት በማድረግ የደመራውን ሥነ ሥርዓት በበላይነት ይመራል፤ ያቀናጃል።
የገዳማትና የአድባራት ሰንበት ት/ቤት መዘምራን በተቀናጀ መልኩ መዝሙራዊ ትዕይንት ያሳያሉ፤ በዓሉ ብሔራዊ ይዘት ያለው በመሆኑ የተለያዩ እንግዶችና ባለሥልጣናት እንዲሁም የውጭ ቱሪስቶች ይሳተፉበታል።
በዓሉን በተመለከተ ስብከተ ወንጌልና የተለያዩ መንፈሳዊ መልእክቶች ይተላለፋሉ።
እንኳን ለደመራ በዓል አደረሳችሁ
አዘጋጅ ፡ መስከረም አበበ
More Stories
የተለያዩ የህክምና መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ሲገለገሉ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ
የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል በደማቅ ስነ ስርዓት በሣጃ ከተማ እየተከበረ ነው
በክረምት ወራት የታየውን ትጋት በበጋውም ለመድገም ቁርጠኞች መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ