መስቀል በጉራጌ!
በመሀመድ ሽሁር ጂጆ
የመስቀል በዓል አጀማመር መሰረት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መገኘት ጋር የተያይዘ ሲሆን ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደሚከበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
ይህ ታላቅ በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ አኗኗርና ወግ በተላበሰ መልኩ የሚከበር ቢሆንም የበዓሉ አከባበር ደረጃና የሚሰጠው ትኩረት ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡
በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ትልቁና ዋነኛው የመስቀል በዓል እንደሆነ ከጉራጌ ባህል እና እሴቶቹ ከተሰኘው መጽሃፍ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሔረሰብ ያለው ማህበራዊ ፋይዳ
የመስቀል በዓል ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦችና ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸው የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሠቦች የሚጠያየቁበት፣ በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች እንዲሁም የተጣሉ ሠዎች የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሠረዝበትና በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው፡፡
ወጣቶችና አዛውንት ደመራ ለማብራት በወጡበት በእድር ደንቦች በአካባቢ ልማት፣ በግብርናና ንግድ ስራዎች ላይ የሚመክሩበት፣ ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁት፣ ጎልማሶች ከአባቶች ኃላፊነት የሚረከቡት፣ የወላድ ማህፀን የሚባረከው፣ ሟርተኞች የሚረገሙት በዚሁ በዓል ነው፡፡
ወላጆች ለበዓሉ የተዘጋጀን ሰንጋ ከፊታቸው አቁመው ሻኛውን በመዳሰስ ትውልዱን ይመርቃሉ /ይባርካሉ/፤ ለአገር ሰላምና ብልፅግና ፈጣሪያቸውን በፀሎት ይለምናሉ፡፡ በጎረቤት እና በአካባቢ ያለን ችግረኛ የሚያስቡበት፣ ለወለደች አራስ የሸሉዳ ስጋ፣ ለተገረዙ ልጆች ጭቅና ስጋ የሚሰጡበት በዓል ነው፡፡
ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ባህላዊ የአዳብና ጨዋታ በተለያዩ የገበያ ስፍራዎችና የጋራ መሠብሠቢያ ቦታዎች በሚኖረው የዘፈንና ጭፈራ ትዕይንቶች በመሳተፍ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሎሚ፣ ብርቱካን እና የሸንኮራ አገዳ በመለዋወጥ ጓደኛ የሚመርጡበትና ለመጻኢ ህይወታቸው መሰረት የሚጥሉበትና የሚወስኑበት በዓል ነው፡፡
በዓሉ በአዲሱ ዓመት የሚሠሩ ስራዎች ተለይተው እንዴት መሠራት እንዳለባቸው የሚመከርበትና የሚታቀድበት በመሆኑ ማህበራዊ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው፡፡
የመስቀል በዓል ዝግጅት
መስቀል በጉራጌ ብሔረሠብ ዘንድ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ መጠን ዝግጅቱም እንዲሁ ከበድ ያለ ነው፡፡ የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረው መስቀል በተከበረበት ዓመት ለሚቀጥለው በዓል አከባበር ማሠብ ይጀመራል፡፡
በዚህ መነሻነትም ከትውልድ ቀዬአቸው ርቀው የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ከትንሽ እስከ ትልቅ ገቢ ያላቸውንም ጨምሮ ለመስቀል በዓል ማሰብ የሚጀምሩትና ገንዘብ የሚያጠራቅሙት በየዓመቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ነው፡፡ በአገር ቤት የሚኖሩ ሴቶች የመስቀልን በዓል ለማክበር ቅቤ ማጠራቀም የሚጀምሩበት ወዲያው መስቀል እንደወጣ ነው፡፡
የመስቀል በዓል በተለይም ሶስትና አራት ወራት ገደማ ሲቀሩት አንስቶ ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ይሄዳል፡፡
በመሆኑም በዚህ ወቅት የሥራ ክፍፍሉ በዕድሜና በፆታ እንደየ አቅሙና ችሎታው ይሠጣል፡፡ የልጆችና የወጣቶች ወንዶች የስራ ድርሻ ለመስቀል በዓል ዝግጅት የሚሆን ፍልጥ እንጨት ማዘጋጀት ሲሆን አባወራዎች ደግሞ ለዕርድ የሚቀርቡ ሰንጋዎች ማድለብና ማዘጋጀት፣ በመስቀል በዓል ወቅት ከብቶች የሚበሉትን ሳር የማዘጋጀት፣ ክልክል የሳር ቦታዎች መከለል እንዲሁም የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ቢለዋዎች ያዘጋጃሉ፡፡
በሌላ በኩል የወጣት ሴቶች የሰራ ድርሻ ቤት የማሳመር ማለትም የተለያዩ ቀለም ባላቸው አፈሮች ቤት መቀባት ሲሆን እማወራዎች በቅድሚያ እንሰት ፍቀው የማዘጋጀት ፣ ጅባ የመሥራት ወይም የመግዛት፣ ለክትፎ ግብዓት የሆኑት እንደ ቂቤ፣ ሚጥሚጣ የማዘጋጀት ሀላፊነት ይወጣሉ፡፡
ከነሐሴ 12 /ከቡሄ/ ጀምሮ ዝግጅቱ እንደገና በአዲስ መልክ ተጠናክሮ ይከናወናል፡፡ ምክንያቱም መስቀል ደርሷልና ነው፡፡
ለአብነትም የመስቀል ደመራ ይደመራል፤ ወጣት ወንዶች የመስቀል እንጨት ጫካ ሄደው መፍለጥና ማዘጋጀት የሚጀምሩት ከቡሄ ጀምሮ እንደሆነና ሌሎች ማንኛውም ነገሮች ሁሉ በትጋትና በንቃት ይከናወናሉ፡፡
መስቀል በጉራጌ አስቀድሞ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገበት በኋላ በዓሉ ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እየተጠቀሙ በታላቅ ደስታና ጭፈራ እንዲሁም ልዩ ልዩ ክንዋኔዎችን በማካሄድ የሚከበር ሲሆን የቀናቱ ስያሜና የሚከናወኑ ተግባራት ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
መስከረም 13 ወሬት የኸና
በመስቀል በዓል ለምግብ ማቅረቢያነት የሚውሉ ቁሳቁሶች ከየግድግዳው የሚወርዱበት ቀን ነው፡፡ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች በጥንቃቄ ፀድተው እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በምግብ ማቅረቢያነት ያገለግላሉ፡፡
በተጨማሪም ሁሉም ቤቱን አፅድቶ አዳዲስ ጅባዎች አነጣጥፎ መስቀልን ለማክበር ዝግጅት የሚጠናቀቅበት ዕለት ነው፡፡
መስከረም 14 ደንጌሳት /የዴጚያ/የዴንጋ እሳት(ይፍት)
ለሁሉም የቤተሰብ አባል በተዘጋጀለት የሸክላ ጣባት የጎመን ክትፎ የሚበላበት ዕለት ሲሆን የዚህ ቀን ሙሉ ወጪ ሴቶች ይሸፍናሉ፡፡
በዚህ ዕለት ማታ በየደጃፉ በልጆች የተደመሩ ደመራዎች ይቃጠላሉ፤ በብሔረሰቡ አጠራር የዴጚያ/የዴንጋ ኧሳት (የባዮች ኧሳት ቀነ) ይባላል፡፡ ስለሆነም ደመራው ሲቃጠል ጎረ ጎረ ፣ ጎረ ጎረ… እያሉ ፈጣሪን ለዚህ እለት ላደረስከን ብለው ሲያመሰግኑ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ያደምቁታል፡፡
መስከረም 15 ወኸመያ /ጨርቆስ/ የእርድ ማይ/
በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ዋናው የመስቀል በዓል የሚከበርበት በእዚህ ዕለት ነው፡፡ በዕለቱም የአባወራዎች ተግባር ጎልቶ የሚታይበት ሆኖ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሁለትና ከዚያ በላይ በመሆን የደለበ ሰንጋ የሚያርድበት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ስጋውን ወንድየው እንዳስገባ ጥሬ ስጋ በቅቤ በመንከር (ጨፉየ) ቀጥሎም ተወዳጁ የጉራጌ ክትፎ ይበላል፡፡
መስከረም 16 ያባንዳ እሳት/ የጉርዝ እሳት
ዋናው መስቀልና ትልቁ /የአባቶች/ ደመራ የሚበራበት ዕለት ሲሆን በአብዛኛው ሀይማኖታዊ ይዘት ጎልቶ ይወጣል፡፡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ቤተክርስቲያን ሄደው ባህላዊ ጭፈራ <<አዳብና>> የሚጨፍሩበትና ሀይማኖታዊ ሥርዓት የተከተለ ደመራ የሚቃጠልበት ቀን ነው፡፡
ወጣቶቹ ከጭፈራ ቦታቸው ወደ ቤት ከተመለሱ በኃላ ወደ ማታ አካባቢ ዋናው ዳመራ በየአካባቢው ይቃጠላል፡፡ በዳመራው ስርም ባህላዊ ጭፈራ ይደምቃል፣ ይጠጣል፡፡ ከዚህ ሁነት በኋላ ሁሉም ወደ ቤቱ ገብቶ በተዘጋጀለት ጣባ ክትፎ ይመገባል፡፡
መስከረም 17 ንቅ ባር/ የከሰል ማይ
ከለሊቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በአንድ አጥቢያ የሚተዳደሩ ዕድርተኞች ደመራ ወደ ተቃጠለበት ቦታ በመሰብሰብ ቃለ መሀላ በማስገባት አዲስ የአካባቢ ዳኛ የሚሾምበትና ያለፈው ርክክብ የሚያደርግበት፣ አዲስ የአባልነት ጥያቄ የሚቀርብበትና ምዘገባ የሚካሔድበት ዕለት ነው፡፡
መስከረም 18 የፊቃቆ ማይ
ሴት ልጃገረዶች የተለያዩ የሥፌት ጌጣ ጌጦች /ዕቃዎች/ ለማዘጋጀት የሚረዳ ሰንደዶ ለቀማ የሚጀመርበት ዕለት ሲሆን በየመንደሩ ልጃገረዶች ባህላዊ ዜማ እያዜሙ ስንደዶ ለቀማ ያደርጋሉ፡፡
ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 23 <<የጀወጀ/ የጀወቸ>>
ዕለቱ አማትና አማች የመጠየቂያ ጊዜ ነው፡፡ ሴት ልጆች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ ለአባቶቻቸው ባርኔጣና ጭራ ሲይዙ ባሎቻቸው ደግሞ ሙክት በመያዝ ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸው የአብራካቸው ክፋይ የሆኑትም ልጆቻቸው በወላጆቻቸው የሚመረቁ ሲሆን በጠቅላላ አማቾቻቸው ዘንድ ትልቅ ክብርና ሞገስ ያጎናፅፏቸዋል፡፡
ባህላዊ የመስቀለ በዓል ጨዋታ <<አዳብና>>
አዳብና ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ባሉት ቀናት ውስጥ በተለያዩ የገበያ ቦታዎችና አቢያተ-ክርስቲያናት የሚከወን የወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ ስነ- ስርዓት ነው፡፡
በዚህ ሰነ- ስርዓት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከየትውልድ ቀዬያቸው ርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማዶች፣ አብሮ አደጎች ተገናኝተው ናፍቆታቸውን ይወጣሉ፤ የሰውም ሆነ የጥበብ ናፍቆት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክብ እየሰሩ የሚዘፍኑ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ዜማና ዳንኪራ በሚደምቀው በዚሁ የአዳብና ጭፈራ ወቅት የትዳር ጓደኛ የመምረጥ ስራ ይከናወናል፡፡
ወንዱ ልጅ ለጭፈራ ከወጡት ኮረዳዎች መሀከል ቀልቡ ካረፈባት ልጅ የሎሚ ስጦታ በመስጠት /ወርውሮ/ በመምታት ለትዳር የምትሆነውን ልጅ በባህሉ መሠረት ያጫል፡፡ በአዳብና ከሚከወናወት የተለያዩ ባህለዊ ጨዋታዎች መካከል በወንዶች ብቻ የሚከወን የዝላይ ትዕይንትም አለ፡፡
ሌላው የሙየቶች ክዋኔ ጥበብ አንዱ ነው፡፡ ሙየቶች ለአዳብና ጭፈራ ከሚወጣው የክዋኔው ታዳሚ ለየት ያለ ቋንቋ፣ ዜማና ዳንኪራ ያለው ክዋኔ ጥበብ የሚያቀርቡ ማህበረሠብ ሲሆኑ ወደ አናታቸው በአደይ አበባ የተሽቆጠቆጡ ልምጭ ይዘው መሪያቸውን እየተከተሉ ሲያዜሙና ሲጨፍሩ ይስተዋላሉ፡፡
በአጠቃላይ በመስቀል ወቅት የሚከናወኑ ባህላዊ መስተጋብሮችና ትዕይንት በተለይም ለሁለቱም የጉራጌ ዞኖች ቱሪዝም እድገት ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በምስራቅ ጉራጌ ዞን በአለም ቅርስነት ከተመዘገበው ጢያ ትክል ድንጋይ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ጀምሮ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፖርክ፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማትና መስጅዶች እንዲሁም ውብና ማራኪ የሆኑ መልክአ ምድሮችን የያዙትን ጉራጌና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖችን የመጎብኘት እድልን ይፈጥራል፡፡
መልካም በዓል!
More Stories
ፓርቲው በየወቅቱ የሚያዘጋጃቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የአባሉን የመፈፀም አቅም እያጎለበቱ እንደሚገኙ ተገለጸ
በህገ-ወጥ የንግድ ስራዎች የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በህጋዊ መንገድ የሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑን አንዳንድ የአርባምንጭ ከተማ ነጋዴዎች ገለፁ
የቀይ አፈር ሙሉ ወንጌል ነህምያ የልጆች ልማት ከደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ሕፃናት መምሪያ ጋር በመተባበር “የዎና ናና” የህፃናት ልማት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በዲመካ ከተማ ተካሂዷል