የቱርሚ ወይጦ 120 ነጥብ 8 ኪሜ የአስፋልት መንገድ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ግንባታው የተጓተተው የቱርሚ ወይጦ 120 ነጥብ 8 ኪ.ሜ የአስፋልት መንገድ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት አስተዳደር መምሪያ አስታወቀ።
የፕሮጀክቱን መጓተት ችግሮች በመፍታት ግንባታውን በ2 ዓመት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ የገለጸው የግንባታው ተቋራጭ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሶ የክፍያና የነዳጅ አቅርቦት ችግሮች ያሰጉኛል ብሏል።
የአርብቶ አደሩን የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ለማቃለል በሚል በ2013 ዓ.ም በፌደራል መንግስት በጀት ግባታው የተጀመረው የቱርሚ ወይጦ 120 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሳይጠናቀቅ አራት አመታትን አስቆጥሯል።
ራማ ኮንስትራክሽን በተሰኘ የግል የግንባታ ተቋራጭ የተጀመረው ፕሮጀክት መጓተት ተደጋጋሚ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል።
በመሆኑም በቅርቡ መንግስትና ተቋራጩ መካከል በተደረገ ውይይት እንቅፋት የነበሩ ተግዳሮቶች በመፈታታቸው ፕሮጀክቱ ዳግም ስራውን የጀመረ ሲሆን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው።
ከወር በፊት ዳግም የግንባታው መጀመርን ተከትሎም በስፍራው ምልከታ ያደረጉት በደቡብ ኦሞ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጩንጩሎ፥ የቱርሚ ወይጦ የአስፋልት መንገድ የአርብቶ አደሩ አካባቢ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መሳለጥ ባለፈ ፈርጀ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ በረከት የሚያመጣ መሆኑ ታምኖ የተጀመረ ነዉ ብለዋል።
ሆኖም ግን በተለያዩ ምክንያቶች የፕሮጀክቱ ግንባታ ለዓመታት ሲንጓተት መቆየቱን ጠቅሰው ይህም ከፍተኛ የህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምንጭ ሲሆን መቆዬቱንም አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ ያጋጠሙትን ችግሮች እንዲቀርፉ በቅርቡ መንግስት የወሰደው የመፍትሄ እርምጃ የመንገዱ ግንባታ በአዲስ መልክ እንዲጀመር አስችሏል ያሉት ኃላፊው፥ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በመምሪያው በኩል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንደሚደረግ በመግለጽ ለስኬታማነቱ የአካባቢው ማህበረሰብ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።
ፕሮጀክቱን እያከናወነ በሚገኘው ራማ ኮንስትራክሽን የቱርሚ ወይጦ መንገድ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂኒየር ስንታየሁ ማሞ፤ ከአራት አመታት በፊት ስራው የተጀመረውና 120.8 ኪሜ የሚሸፍነው የመንገድ ስራ ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ በተቀመጠለት ጊዜና በጀት ማከናወን ሳይቻል ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ዳግም የተጀመረው ፕሮጀክት በ2 ዓመት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከስምምነት የተደረሰ መሆኑን ጠቁመው ቀደም ብሎ ከተጠናቀቀው የአፈር ሙሌት በኃላ የሚቀጥሉ የ 7 ድልድዮችና የቱቦ ቀበራን ለማከናወን 3 ንኡስ የስራ ተቋራጮች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
አስፈላጊ የግንባታ ግብዓቶች በማሟላት በምሽት ጭምር ስራዎች እየተቀላጠፉ እንደሆነ የሚገልጹት ማናጀሩ፤ በእስትራክቸራል ስራዎች የአንድ ወር አፈጻጸም ከ9 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ ጥቅል አፈጻጸሙ 26.8 በመቶ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የፕሮጀክቱ ስራ ሳይንጠባጠብ እንዲቀጥል በተቋራጩ በኩል ጠንካራ ቁርጠኝነት መኖሩን ጠቁመው፤ ሆኖም ግን ከክፍያና ከነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች ስጋት ያላቸው መሆኑንም አልሸሸጉም።
ስለሆነም በዚህ ረገድ ያሉ ተግዳሮቶች እንቅፋት እንዳይሆኑ መንግስት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በኦሜጋ የግንባታ አማካሪነት የሚከናወን ሲሆን በመጭው 2019 ዓ.ም ሰኔ ወር ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ የሺመቤት ዋሴ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በያሆዴ በዓል ወቅት የሚደረገው ሲምፖዚየም ለሀገር ልማትና አንድነት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
በልዩ ልዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ወደ ትምህርት ገበታ ሊመጡ ያልቻሉ ተማሪዎች መደገፍ እንደሚገባ ተጠቆመ
ጥራትና ወቅታዊነት ላይ ትኩረት ያደረገ የዕቅድ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ