የመሬት መጠቀሚያ ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፈል እንደሚገባ ተገለፀ

የመሬት መጠቀሚያ ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፈል እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህብረተሰቡ የመሬት መጠቀሚያ ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት የላስካ ዙሪያ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በባስኬቶ ዞን የላስካ ዙሪያ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የአርሶ አደሩ ማሕበረሰብ የመሬት መጠቀሚያ ግብር ዕቅድ አፈፃፀምና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የመልካም አስተዳደር እና የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው ህብረተሰቡ መልሶ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ መክፈል ሲችል መሆኑን በመድረኩ የተገኙት የላስካ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ግርማ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን የመሬት መጠቀሚያ ግብር በታማኝነት በመክፈል ወደ ተሟላ ልማት መሸጋገር እንደሚቻል የላስካ ዙሪያ ወረዳ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተመስገን አዘኔ ገልፀው፥ ገቢ መሰብሰብ የሁሉም ድርሻ መሆኑን አውቀን በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝባችንን ለመልማት ፍላጎት ምላሽ ልንሰጥ ይገባናል ብለዋል።

የላስካ ዙሪያ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሞዝ ካንሶ፥ አርሶ አደሩ በወቅቱ በሚጠቀመው መሬት ልክ ግብር እንዲከፈል ማድረግ ግዴታ መሆኑን ተናግረ፥ ባሳለፍነው በጀት ዓመት 6 ሚልዮን 895 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 4 ሚልዮን 399 ሺህ 895 ብር መሰብሰብ እንደተቻለም ባቀረቡት ሪፖርት አመላክተዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት የወረዳው መንግሥት ከተለያዩ ገቢዎች ማለትም ከትምህርት፣ ከጤና እና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 115 ሚልዮን 362 ሺህ 438 ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ ደሞዝ አብራርተዋል ።

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት ለዕቅዱ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ቀበሌያት የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ ፡ ዓቢይ ይኼይስ – ከሳውላ ጣቢያችን