“ማሽቃሮ” ለትውልድ እንዲሸጋገርና ይበልጥ ማስተዋወቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

“ማሽቃሮ” ለትውልድ እንዲሸጋገርና ይበልጥ ማስተዋወቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ማሽቃሮ” ለትውልድ እንዲሸጋገርና ይበልጥ ማስተዋወቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑን የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ተናገሩ።

የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሮ”ን ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ የካፋ ብሔር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ በርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ትውፊቶች ያሉት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የዘመን መለወጫ ወይም “ማሽቃሮ” መሆኑን ጠቁመዋል።

ማሽቃሮ የክረምት ወቅት አልቆ በጋ መግባቱንና የዘመን መለወጥን ተከትሎ የሚካሄድ ኩነት መሆኑን የገለጹት አቶ እንዳሻው፥ ካፋዎች የአዝመራን ወቅት ተንተርሰው የሐምሌ ወር በገባ ከአምስተኛው ቀን ጀምሮ 77 ቀናትን በመቁጠር ያከብራሉ ብለዋል።

ማሽቃሮ ከበርካታ ዘመናት በፊት እየተከበረ የቆየ ቢሆንም በመሃሉ ተቋርጦ ቆይቶ ከ1998 ጀምሮ እስካሁን በየዓመቱ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን ህዝቡ በባለቤትነት ይዞ ለትውልድ እንዲያሸጋግርና በይበልጥ ማስተዋወቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም እንዲያግዝ ምሁራንን ያካተተ የባህል ምክር ቤት በማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው ማሽቃሮ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተመረቀበትና የካፋ ነገስታት ዘውድና መቀመጫን ከ128 ዓመታት በኋላ ወደ ካፋ በተመለሰበት ማግስት የሚከበር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ በሀብታሙ ታደሰ- ከቦንጋ ጣቢያችን