የስንዴ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

የስንዴ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

በኣሪ ዞን ደቡብ ኣሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም/FSR/ በጀት ድጋፍ አሲዳማ መሬት ሰፋፊ ሰርቶ ማሳያ ተግባራት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን የ2017/2018 ዓ/ም የመኸር ማብሰሪያ ፕሮግራምም ተካሂዷል።

በ75 ሄክታር መሬት ላይ “ዋኔ” በተሰኘ የስንዴ ምርጥ ዘር በሸንጋማ ቀበሌ እየተከናወነ እንደሆነ የኣሪ ዞን የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተግባሩ በስፍራው በመገኘት ምልከታ አድርገዋል።

የኣሪ ዞን ግብርና መመሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ እንደ ዞን 150 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ምርጥ ዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመው፥ ከዚህ በፊት የስንዴ ምርጥ ዘር ከሌላ አካባቢ በማምጣት አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ይደረግ ነበር ይህ በትጉህ አርሶ አደሮች መቀየር አለበት ብለዋል።

የኣሪ ዞን ም/አስተዳዳሪና ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገረመው ኃ/ማርያም የአርሶ አደሩ ምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ሁላችንም መረባረብ እንደሚገባ አመላክተው፥ ምርታማነት የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብና በዚህ ልክ ግንዛቤ መፍጠር በዘርፉ ያለው ውጤት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲረጋገጥ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል ።

በመርሐ ግብሩ የገኙት የጂንካ ግብርና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሌ ዮሴፍ፥ የምርምር ተቋማት በክልሉ ያለውን የግብርና ምርጥ ዘር ችግር እንዲቀርፉ ተልዕኮ ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

ይህ ተግባር በሁሉም አካባቢ እየተተገበረ ሲሆን በኣሪ ዞን ደቡብ ኣሪና ሰሜን ኣሪ ወረዳዎች 150 ሄክታር ምርጥ ዘር የስንዴ ብዜት እየለማ ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፎችን የሚሰጡ ባለሙያዎችን መድቦ ለውጤታማነቱ እየሠራ ስለመሆኑም ዶ/ር ተክሌ ገልፀው በየዓመቱ የምርጥ ዘር ብዜት ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱንም አስረድተዋል።

የኣሪ ዞን መንግስት ረዳት ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ፓለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማንኩል ሳሎ በአካባቢው ለስንዴ ልማት ልሆኑ የሚችሉ የመሬት አካላትን በሙሉ አርሶ አደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያለማ አሳስበዋል።

የአካባቢው የአየር ፀባይ ለስንዴ ልማት ምቹ በመሆኑ ለምርጥ ዘር ብዜቱ ተመራጭ ያደርገዋል ተብሏል።

የአካባቢው አርሶ አደሮችም በምርጥ ዘር ብዜቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የምርጥ ዘር ብዜቱ ከክልል ጀምሮ በተዋረድ እስከ ዞንና ወረዳ እንዲሁም የጂንካ ግብርና ምርምር ተቋም በጋራ እያካሄዱ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል ።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን