የካፋ ህዝብ ለዘውድ ያለው አክብሮት ከመሪው ጋር ላለው መልካም ግንኙነት ማረጋገጫ ነው – ዶ/ር ዘገየ ወልደማርያም

የካፋ ህዝብ ለዘውድ ያለው አክብሮት ከመሪው ጋር ላለው መልካም ግንኙነት ማረጋገጫ ነው – ዶ/ር ዘገየ ወልደማርያም

ሀዋሳ፡ መስከረም 11/2018 ዓ.ም (ደረቴድ) የካፋ ህዝብ ለዘውድ ያለው አክብሮት ከመሪው ጋር ላለው መልካም ግንኙነት ማረጋገጫ ነው ሲሉ የካፋ ታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ዘገየ ወልደማርያም ገለጹ፡፡

ተመራማሪው የካፋ ምሁራን ማህበር የ2017 ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በካፈቾ ታሪክ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል።

የካፋ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረውን ድርሻ፣ የስልጣኔ እንዲሁም ሌሎችን ማህበረሰባዊ እውነታዎች የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል።

በጥናታቸውም በኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማመላከት የመፍትሔ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል።

የተለመደው የታሪክ አፃፃፍ የተፃፉ ሰነዶች ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆኑ፤ የማህበረሰቡን፣ ባህል፣ እሴትና የካርታ መረጃዎችን በግብዓትነት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ተመራማሪው ለአብነት አንስተው ማብራሪያ ከሰጡባቸው ታሪካዊ ሀብቶች መካከል አንዱ የካፋ ነገስታት ዘውድ ነው።

ማህበረሰቡ በበቂ ሁኔታ ያልተፃፈና ያልተተነተነ ታሪክ ያለውና የዘመናዊ የመንግስት መዋቅር መሠረት ከሆኑ እውቀቶች አንዱ ዘውድ መሆኑን አመላክተዋል።

የነገስታቱ ዘውድ የአካባቢው ሉዓላዊነት ምልክት እንደሆነ በመግለጽ ፤ የሰውንና የመሬቱን ምርታማነት እንዲሁም የህዝቡን ውጤታማነት የሚያረጋግጥ የመሪዎች መለያ መሆኑን አብራርተዋል።

አሁን ላለው ትውልድም ከፍተኛ የስነ-ልቦና ፋይዳ እንዳለው ዶክተር ዘገየ ተናግረዋል።

ህዝቡ ሀገሩ ሰላም መሆኑን እና አስተዳዳሪው መንግስት ኃላፊነት ላይ በብቃት እንደሚገኝ የሚያረጋግጥ እንደሆነ በትንታኔ አቅርበዋል።

አሁን በዘመነው ዓለም ታሪክ ሲፃፍ አንዱ ማረጋገጫና ታሪክን ለትውልድ ለማስተላለፍ ዘውድ ሁነኛ ሀብት መሆኑን ዶክተር ዘገየ ገልጸዋል።

ህዝቡ ለዘውድ ያለው አክብሮትና የሚሰጠው ግምት ከመሪው ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት ማሳያ ሆኖ ያገለግላል ሲሉ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን