በቦንጌ ሻምበቶ የሚከበረውን የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በቦንጌ ሻምበቶ የሚከበረውን የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ከመስከረም 12-13/2018 ዓመተ ምህረት በቦንጌ ሻምበቶ የሚከበረውን የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ እምቢበል ወንድሙ የዘንድሮው የብሔሩ ዘመን መለወጫ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበትና የካፈቾ ብሔር የመጨረሻው ንጉስ ጋኪ-ሻሮች ዘዉድና መቀመጫ በተመለሰበት ወቅት የሚከበር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

ይህ በልዩ ደስታ የሚከበር በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቦንጋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ተስፋዬ አበበ በዓሉ የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ እንደመኖሩ መጠን፥ የስርቆትና ሌሎችም ወንጀሎች እንዳይከሰቱ በከተማው ስድስቱም ቀጠናዎች የፖሊስ አባላት፣ ደንብ አስከባሪዎችና የፓትሮል ቅኝቶችን በማቀናጀት ከሮንድ ጥበቃ ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በከተማው አልፎ አልፎ ባዶ የሆኑ ቤቶችና ባለቤቶቻቸው ሩቅ ሆነው የሚከራዩ ቤቶች ለስርቆት መበራከትና ወንጀል መከሰት ምክንያት እየሆኑ መጥተዋል ብለው ፤ በዚህ ዙሪያ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የእንግዶች መብዛትን ተከትሎ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በበዓል ወቅት ለጸጥታ ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮች በሚስተዋሉበት ወቅት ለጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት በዓሉ በሠላም እንዲከበር ማህበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ለመላው የካፋ ህዝብ እንኳን የብሔሩ ዘመን መለወጫ ለሆነው “ማሽ ቃሬ ባሮ” በሠላም አደረሳችሁ ሲሉም የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ምኞት ወ/ሚካኤል – ከቦንጋ ጣቢያችን