ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በዓላማቸው መነሻ የማህበረሰብ ኑሮ በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 11/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በዓላማቸው መነሻ የማህበረሰብ ኑሮ በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በላቸው ገለጹ።

የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ የነበረው የ20 ዓመት ቆይታ ማጠናቀቂያ መርሐ-ግብር መድረክ ተካሂዷል።

በህዝብ ስም በርካታ ሀብት አሰባስበው ወደ ተግባር የሚገቡ የተራዶ ድርጅቶች ቢኖሩም በተጨባጭ የማህበረሰቡን ኑሮ በሚያሻሽል ተግባር ላይ የማያውሉ መኖራቸውን ኢንጂነር በየነ በላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ረገድ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ገዋታ አካባቢ ፕሮግራም ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን በማከናወን በህብረተሰቡ ላይ የሚታይ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

ድርጅቱ በዞኑ የጀመረውን በጎ ተግባር ማስቀጠል የሚችልበት ሁኔታ እንዲኖር ጠይቀው ፤ የወረዳው ህዝብ ድርጅቱ በቆይታው ያሳካቸውን ውጤታማ ሥራዎች በቁርጠኝነት ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ያለፉት 20 ዓመታት በወረዳው የፅናት የለውጥና የስኬት ጊዜያት ናቸው ያሉት በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ኦፒሬሽን ዳሬክተር አቶ ሳሙኤል ጥላሁን ድርጅቱ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀይሯል ብለዋል።

ፕሮግራሙ በወረዳው ስራ ሲጀምር የብዙ ህፃናት ሕይወት ችግር የተሞላ፣ የምግብ ዋስትና ሁኔታ አስቸጋሪ ትምህርት ቤቶች ጥቂት በመሆናቸው ፤ የመማሪያ ክፍሎች የተጨናነቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

ንፁህ ውሃ በቅርብ ርቀት ባለመኖሩ ህፃናትና ሴቶች ሩቅ መንገድ በመጓዝ ለተለያዩ ጉዳቶች ከመዳረጋቸውም ባሻገር ከትምህርት ገበታቸው ይቀሩና ያቋርጡ ነበር ብለዋል።

ድርጅቱ ይህንን ችግር በጥናት በመለየት በሰራው ስራዎች ዓመቱን ሙሉ በቂ ምግብ የማግኘት ዕድል ያላቸው ቤተሰቦች ሽፋን ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 54 በመቶ ማድረስ መቻሉን ነው የገለጹት።

በወረዳው ያለውን የትምህርት ተሳትፎ ከ52 ወደ 72 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በወረዳው ከ86 ሺህ በላይ ልጆችና ቤተሰቦቻቸው በትምህርት፣ በጤና በሥነ-ምግብ፣ በንፁህ ውሃ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎችም ዘርፎች ተደራሽ ሆነዋል ብለዋል።

የካፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ ፕሮግራሙ በጤናው ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸው ፤ ድርጅቱና አመራሩን እንዲሁም ሠራተኞችን አመስግነዋል።

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን