ሀዋሳ፡ መስከረም 11/2018 ዓ.ም (ደረቴድ) በካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ የ18ቱ የካፋ ነገስታት መካነ-መቃብር (ሾሻ ሞጎ) ላይ የሚከናወኑ ባህላዊና ታሪካዊ ኩነቶች ለዓለም መተዋወቅ እንዳለባቸው የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡
በወረዳው በተከበረው የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሮ” አከባበር ላይ የተገኙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲህ አይነት ታሪካዊና ባህላዊ ኩነቶች ሊተዋወቁ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የካፋ ዞን አስተዳደር በበኩሉ ስፍራው ይበልጥ እንዲለማና እንዲተዋወቅ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።
በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ረዳት የመንግስት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ የካፋ ማህበረሰብ በዓሉን ማክበሩ ትውልዱ በራሱ ታሪክና ባህል እንዲኮራ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ሾሻ ሞጎ በርካታ ያልተነገሩ፣ ሌላኛው ዓለም ሊያውቃቸው የሚገባቸው ባህላዊና ታሪካዊ ክዋኔዎች ያሉበት መሆኑን የገለጹት አቶ በላይ ዘንድሮም በስፍራው ይህንን በዓል ማክበራቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
መንግስት የማህበረሰቡ ባህል፣ ወግና ትውፊት ጎልቶ እንዲታይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለው ፤ በአካባቢው የሚስተዋሉ የመሰረተ-ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በህብረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በበዓሉ ላይ የታደሙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ማሽቃሮ የካፋ ማህበረሰብ ልዩ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ሾሻ ሞጎ ላይ የሚከናወኑ ባህላዊና ታሪካዊ ኩነቶች ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ መተላለፋቸው ማህበረሰቡ ለባህሉና ለታሪኩ ያለውን ትልቅ ስፍራ ያሳያል ብለዋል።
ይህ ስፍራ ከአካባቢው አልፎ ለሀገር ቅርስ እንዲሆን የሚያስችሉት በርካታ ታሪኮችን የያዘ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢብራሂም ፤ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች ሊሰሩበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ዘንድሮ የማሽቃሮ በዓል ትውልዱ የቀደሙ አባቶችን ታሪክ በተገቢው እንዲያውቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ማሳያው የጥንት ነገስታት ይጠቀሙበት የነበረውና ከ120 ዓመታት በፊት የተወሰዱ የካፋ ነገስታት ዘውድና መቀመጫ መመለሳቸው መሆኑን አንስተዋል።
የነገስታቱ መቃብር የሚገኝበት ስፍራ (ሾሻ ሞጎ) ከዞኑ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች አንዱ ሆኖ መመዝገቡን የገለጹት አቶ እንዳሻው ፤ ስፍራውን ለማልማት ይሰራል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ጠንካራ የጤና ልማት ስርአት በመዘርጋት የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በቡና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች የውሃን ሀብት ከብክለት በመጠበቅ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም