ጠንክሬ ማጥናቴና ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀሜ ለዚህ ውጤት አብቅቶኛል – ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ይስሐቅ ሰብስቤ
ሀዋሳ፡ መስከረም 10/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጠንክሬ ማጥናቴና ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀሜ ለዚህ ውጤት አብቅቶኛል ሲል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ይስሐቅ ሰብስቤ ተናገረ፡፡
በኮሬ ዞን የዶንሶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የሆነው ይስሐቅ ሰብስቤ፤ ጊዜዬን በአግባቡ በመጠቀሜና ጠንክሬ በማጥናቴ 568/600 ውጤት ማስመዝገብ ችያለሁ ብሏል።
ለውጤቱ መሳካት የእሱ ጥረት ብቻ ሳይሆን የቤተሰብና የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር የሚናገረው ተማሪ ይስሐቅ፤ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በሚገባ መጠቀምና በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል።
የተማሪው ወላጅ አቶ ሰብስቤ ሽፈራው፤ ይስሐቅ ከልጅነቱ ጀምሮ ለትምህርት ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረውና የልፋቱን ውጤት ማግኘት እንደቻለ ነው የሚገልጹት።
እንደ ወላጅ በሚያስፈልገው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚናገሩት አቶ ሰብስሴ፤ ሁሉም ወላጅ ለልጆቹ በትምህርት የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የኮሬ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰረበ አሻግሬ፤ በተማሪ ይስሐቅ ሰብስቤ በተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ሁሉም በርትቶ ከካጠና ከዚህም በላይ የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግብ ይችላል የሚሉት አቶ ሰረቤ፤ ሌሎች ተማሪዎችም የተማሪ ይስሐቅን አርአያ በመከተል ለላቀ ስኬት መትጋት እንዳለባቸው ነው የገለፁት።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የመማር ማስተማር ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ፤ በክልሉ በመደበኛ፣ በማታ እና በግል 57 ሺህ ተማሪዎች ተፈትነው 4.6 በመቶ የሚሆኑት የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ማምጣት እንደቻሉ ነው የተናገሩት።
ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በተወሰነ መልኩ መሻሻል ማሳየቱንና በክልሉ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 568/600 ሲሆን ይህም የተማሪ ይስሐቅ ሰብስቤ እንደሆነና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ጠንካራ የጤና ልማት ስርአት በመዘርጋት የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በቡና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች የውሃን ሀብት ከብክለት በመጠበቅ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም