በፈተና ውስጥ በመትጋት፣ ‘አዲስ ሰው’ መሆንና መፈጠር እንዳለ ደራሲ ጠበቃና የማህበረሰብ አንቂ ዳግማዊ አሰፋ አሳይቶናል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

በፈተና ውስጥ በመትጋት፣ ‘አዲስ ሰው’ መሆንና መፈጠር እንዳለ ደራሲ ጠበቃና የማህበረሰብ አንቂ ዳግማዊ አሰፋ አሳይቶናል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ


‎በፈተና ውስጥ በመትጋት፣ ‘አዲስ ሰው’ መሆንና መፈጠር እንዳለ ደራሲ ጠበቃና የማህበረሰብ አንቂ ዳግማዊ አሰፋ አሳይቶናል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ደራሲው 3ኛ ስራውን እና “የተፈቱ ሰንሰለቶች” የተሰኘ መጽሐፉን በአርባምንጭ ከተማ አስመርቋል።

‎ደራሲው የሰውን ድጋፍ የሚሻ ነገር ግን ተስፋ ሳይቆርጥ ከባዱን ጊዜ አሸንፎ “አዲስ ህይወት” የተሰኘውን መጽሀፉን በመጀመሪያ አምጦ ወለደ።

‎በቀጣይም “ከማዕዘኑ ወዲህ” የተሰኘውን መፅሐፍ ለአንባቢ በማቅረብ ይቅርታን በተግባር አሳይቷል ደራሲና የህግ ባለሙያ ዳግማዊ አሰፋ።

‎ዳግማዊ “የተፈቱ ሰንሰለቶች” የተሰኘውን ሶስተኛውን መጽሀፍ በአርባምንጭ ከተማ ባስመረቀበት ወቅት ለታዳሚዎች፤ በህይወት መኖር ተስፋ፣ በጎ ነገርና ለውጥ አለው ስለሆነም ምንም ሁኔታ ቢያጋጥመን በከባድ ነገር ውስጥ ብናልፍም ህይወት እስካለ ለሰው የሚተርፍ ነገር መስራት እንደሚቻል ይሞግታል።

‎የህይወት ጎዳና አስተማሪ መሆኑን ፣ ወንድማማቾች አስቸጋሪ ወቅቶችን በፍቅር አብረው እንዲሻገሩ፣ በውስጣችን የሚገኙ ቁርሾዎችን በይቅርታ እንድናልፍና በበጎ እንድንቀበል ይመክራል።

‎በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ በጽናት የቆመው ዳግማዊ፤ በማንኛውም ነገር ውስጥ ትልቁ ሰንሰለት ጥላቻ፣ ቂም እና በቀል እንደሆነ ያነሳል።

‎ህይወት እስካለ ተስፋ አለ ማለትን የህይወቱ ፍልስፍና ያደረገው ዳግማዊ፤ በመኖር ውስጥ ደግሞ ያለንን ነገር በመስጠት ሊሆን ይገባል ሲል በመጽሀፉ ምረቃ ላይ አንስቷል።

‎በመፅሀፍ ምረቃ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፤ “የተፈቱ ሰንሰለቶች” መፅሀፍ በብዙ መልኩ ካሰሩን የህይወት ውጣ ውረዶች ለመፈታት መበርታት፣ በፅናት መቆም እና መትጋትን ያስተምረናል።

‎የሰው ልጅ ሰላም ሊሆን የሚችለው ለሰው ሁሉ የይቅርታ ልብ ሲኖረው እንደሆነ መጽሀፉ ይነግረናል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ዳግማዊ በፈተና ውስጥ በመትጋት አዲስ ሰው መሆንና መፈጠር እንዳለ አሳይቶናል ብለዋል።

‎ከቂም በቀልና ከጥላቻ በመውጣት በይቅር ባይነት መንፈስና በመተባበር ሰው ተኮር ስራዎችን ልንሰራ እንደሚገባና በፍቅር ጥላቻን በመርታት በየትኛውም የማህበራዊ ሚዲያ አብሮነትንና አንድነትን የሚያሰፍኑ መልዕክቶች ላይ ወጣቱ ማተኮር እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

‎የጋሞ አባቶችን የይቅርታ ልብ እና የሰላም ተምሳሌትነት ለሁሉም ለማድረስ ወጣቱ ሊተጋ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ መክረዋል።

‎”የተፈቱ ሰንሰለቶች” ምረቃ መርሐ ግብር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁ ከበደ፣ የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር መስፍን መንዛ፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ደምስ አድማሱን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የከተማው ወጣቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን