የሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ መገለጫ የሆነው አዳብና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

የሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ መገለጫ የሆነው አዳብና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

አዳብና በሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ባሉት ቀናት ውስጥ በተለያዩ የገበያ ቦታዎችና ሀይማኖታዊ ስፍራዎች በወጣት ሴቶችና ወንዶች የሚከበር የአደባባይ ባህላዊ ክዋኔ ነው፡፡

በምስራቅ ጉራጌ ዞን የሶዶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ መለሰ በሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ የወጣቶች መተጫጫ የሆነው አዳብና በምዕራቡ አለም መጤ ባህሎች ሳይበረዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍና በቱሪዝሙ ዘርፍ የማይዳሰስ የአለም ቅርስነት እውቅና እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አዳብና መስቀል ከዋለበት መስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 የሚከበር ሲሆን ልጃገረዶች እና ወጣት ወንዶች የሚተጫጩበት ባህል እንደሆነ ገልጸዋል።

ባህሉ በውስጡ ከያዘው ባህላዊ ክዋኔና ትዕይንት ባለፈ በዋናነት ወንዱ አይኑ ያረፈባት ሴት ከተመለከተ ሎሚ ወርውሮ ሲመታት ሎሚውን የምታነሳው ከሆነ ፈቃደኛ መሆኗን በማሳየቷ ጉዳዩ እስከ ቤተሰብ በመውሰድ ይጠናናሉ ነው ያሉት።

የማህበረሰቡ የጋብቻ ባህል በሚፈቅደው መሰረት ወደ ሴቷ ቤት ሽማግሌ ተልኮ ተቀባይነት ካገኘ በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ ጋብቻ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲመሰረት የሚያግዝ ድንቅ ባህል መሆኑን አስረድተዋል።

ሊቀ ሂሩያን ብርሃኑ ዋካ እና አቶ አማረ ሀይሉ በሰጡት ማብራሪያ አዳብና አዳምና ሄዋን የሚል ጥሬ ትርጉም የያዘ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ለመተጫጨት የሚገናኙበት እንዲሁም በተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ጥንተ መሰረት ያለው የማህበረሰቡ ድንቅ ባህል ነው ብለዋል።

በአዳብና ስነ-ስርዓት የክረምቱ ጭጋግ ተገፎ መስከረም ሲጠባ ሴት ልጃገረዶች ጸጉራቸውን በመሰራት መልካም መዓዛን ለመፍጠር አደስና ቅቤ ተቀብተው ለበዓሉ የሚሆን ባህላዊ ልብስ በመልበስ ተውበው በየአቅጣጫው “ሀዬ ሀዬ ዬዎ አበቢየ የመስከረሚየ” እያሉ በማዜም የሚገኙበት ሲሆን ወጣት ወንዶችም የሚያጯትን ለመምረጥ ደምቀው የሚወጡበት ባህል መሆኑን አስረድተዋል።

አዳብና በተለያዩ የገበያ ስፍራዎችና ቤተክርስቲያናት ከወጣት ሴቶችና ወንዶች ጭፈራና ሙየቶች ትዕይንት ባሻገር ለየት ባለ አለባበስ የተነፋፈቁ የሚገናኙበት፤ ያላገቡ የሚተጫጩበት፤ አዲስ ሙሽሮች አደባባይ የሚወጡበት፤ የፈረስ ጉግስ የሚከናወንበት፣ ወጣት ወንዶች ለአቅመ አዳም መድረሳቸውን በዝላይ በማሳየት እራሳቸውን የሚፈትሹበት እና ሌሎች በርካታ ባህላዊ ሁነቶች የሚከናወኑበት ቱባ ባህል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ ባህል በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ማለትም በጠለፋና በአላስፈላጊ ዘመናዊነት ተገትቶ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ በመንግስት እና ማህበረሰቡ የጋራ ርብርብ እያንሰራራ ነው ብለው፤ አዳብና በቱሪዝሙ ዘርፍ እውቅና እንዲሰጠው ይበልጥ በማስተዋወቅ ጠብቆ ሊይዘው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ወ/ሪት ጽጌረዳ አሸናፊ፣ አበባ ከበደና ይስሐቅ አዳነ በሰጡት አስተያየት አዳብና ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የወጣቶች የመተጫጫና መገናኛ የአደባባይ ባህል ነው ብለዋል።

ባህሉ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የተለያዩ ባህላዊ አልባሳት በመልበስና ጸጉራቸውን በመሰራት ወደተመረጡ ገበያዎችና ሀይማኖታዊ ቦታዎች በማምራት በጭፈራና በተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች የሚያከብሩትና አዳዲስ ሙሽሮችም ተውበው የሚወጡበት እንደሆነ ገልፀዋል።

አዳብና ወጣቶች ተጠናንተው የሚተጫጩበት ባህል ብቻ ሳይሆን በየአመቱ በጉጉት የሚጠብቁት የክረምቱ ጭጋግ ተገፎ ወደ ብርኃን መሸጋገራቸውን በደስታ የሚገልጹበትና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን የሚያድሱበት ድንቅ ባህል ነው ብለዋል።

ለአዳብና መደብዘዝና መረሳት ዋነኛው ምክንያት ዘመናዊነት በመሆኑ በቀጣይ ወጣቱ በባለቤትነት ባህላዊ ትውፊቱን ሳይለቅ ወደነበረበት ለመመለስ ከሚመለከተው ባለድርሻ አካል በቅንጅት ሊሰራበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አዱኛ ትዕዛዙ – ከወልቂጤ ጣቢያችን