“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህብረታችን አርማ የብልጽግናችን አሻራ ነው” – ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህብረታችን አርማ የብልጽግናችን አሻራ ነው” – ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህብረታችን አርማ የብልጽግናችን አሻራ ነው” ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን በተመለከተ በቦንጋ ከተማ በተደረገ የድጋፍ ሰልፍ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ግድቡ የህብረታችን አርማ የብልጽግናችን አሻራ ነው ብለው፤ ኢትዮጵያ የራሷን ተፈጥሯዊ ሀብት እንዳትጠቀም የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በጋራ በመቆማችን ውስብስብ ችግሮችን መሻገር እንደተቻለ በመጠቆም፤ ከተባበርን የሚያቆመን ኃይል አይኖርም ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በጋራ ስንቆም ከተራራ የገዘፍን ከብረት የጠነከርን ስለመሆናችን ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በደማችንና በላባችን ያጸናነው ህያው የወል ቅርሳችን ነው ብለዋል።

ግድባችንን በወጀብ ሳንናወጥ እንዳጠናቀቅነው ሁሉ በሌሎች የልማት ሥራዎች በፅናትና በአንድነት መቆም እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፤ የዞኑ አስተዳደርና ህዝብ ለግንባታው የቦንድ ግዢና የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች የዞኑ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን