የሥራ ዕድል ፈጠራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገለጸ

የሥራ ዕድል ፈጠራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሥራ ዕድል ፈጠራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደለው የኮሬ ዞን ሥራና ክህሎት ዩኒት አስታወቀ፡፡

የኮሬ ዞን ሥራና ክህሎት ዩኒት የ2017 ተግባር አፈጻጸም ግምገማና የ2018 በጀት አመት የንቅናቄ መድረክ በኬሌ ከተማ አካሂዷል።

የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንዳባ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የሥራ ዕድል ፈጠራ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥን ጨምሮ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና መረጋጋት አስተዋፅኦ አለው።

በተለይ ወጣቶችን በተለያዩ ዘርፎች አደራጅቶ ወደ ሥራ ከማስገባት አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይተን በመፍታት ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

የኮሬ ዞን ሥራና ክህሎት ዩኒት ኃላፊ አቶ በላይ በየነ በበኩላቸው፥ መስራት እየፈለጉ የአቅምና ቦታ ውስንነት ያለባቸውን በመለየት ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ ነው የሚገልጹት።

ለወጣቶች በጊዜያዊና ቋሚ ሥራ ፈጠራ ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ከፍተኛ ናቸው የሚሉት ኃላፊው፥ በቂ ስላልሆነ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የ2017 ተግባር አፈጻጸም እና የ2018 በጀት አመት ዕቅድ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ የመረጃዎች ቅብብሎሽ ማነስና በየጊዜው ስራ ፈላጊዎችን በመለየት ስልጠናዎችን አለመስጠት የሚፈለገውን ያህል እንዳይሰራ አድርጎታል ነው ያሉት ።

በሁሉም ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታትና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የመስራት ሃላፊነት የሁላችንም ሊሆን ይገባል ብለዋል ።

ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን